የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ እጣ የሚወጣበት እና ውድድሩ የሚጀመርበት ቀናት ይፋ ሆነዋል፡፡
የፌዴሬሽኑ የውድድር እና ስነ-ስርአት ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ ከዛሚ ስፖርት ብሄራዊ ጋር ባደረጉት የስልክ ቆይታ እንደተናገሩት የከፍተኛ ሊግ የውድድር ደንቦች እና እጣ ማውጣት ስነስርአት ታህሳስ 9 ቀን 2008 ይካሄዳል፡፡ ለክለቦቹም ጥሪ ተበትኗል፡፡ ውድድሩ ደግሞ ታህሳስ 23 እና 24 ይጀመራል ብለዋል፡፡
ዘንድሮ የሚጀመረው ከፍተኛ ሊግ 32 ክለቦች የሚያሳትፍ ሲሆን ታህሳስ 9 ከክለቦች ጋር በሚደረገው ውይይት በምን ያህል ዞኖች ተከፍሎ ውድድሩ እንደሚካሄድ ፣ ምን ያህል ክለቦች ወደ ፕሪሚየር ሊግ አንደሚያልፉ እና ምን ያህል ክለቦች ወደ ብሄራዊ ሊግ እንደሚወርዱ እንዲሁም ወደ ሊጉ የሚያልፉ ክለቦች እንዴት እንደሚለዩ ይወሰናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አቶ ሰለሞን በስልክ ቆይታቸው እንደተናገሩት የውድድር እና ስነ-ስርአት ኮሚቴው በእቅድ ደረጃ ውድድሩን በ2 ዞኖች ለመክፈል የታሰበ ሲሆን 4 ከለቦች ወደ ፕሪሚየር ሊግ አልፈው የ2009 ፕሪሚየር ሊግ በ16 ክለቦች ለማድረግ ታቅዷል፡፡ እነዚህን ጨምሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የሚያልፉት ክለቦች የሚለዩበት መንገድ በጥሎ ማለፍ (Playoff) ወይም በአንድ ከተማ በሚደረግ ውድድር እንደሚሆን የሚወሰነው ታህሳስ 9 በሚደረገው ውይይት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና 57 ክለቦች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሊግ ታህሳስ 14 የውድድር ደንብ እና ፕሮግራም የማውጣት ስራዎች የሚሰሩ ሲሆን በታህሳስ መጨረሻ ውድድሩ እንደሚጀመር አቶ ሰለሞን ከዛሚ ስፖርት ብሄራዊ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል፡፡
-የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ፌዴሬሽኑ ለውድድሩ የሰጠው ይፋዊ ስያሜ ሲሆን ‹‹ ሱፐር ሊግ ›› የሚባለው በተለምዷዊ አጠራር ነው፡፡