የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ሰርጂዮቪች “ሚቾ” ሚሉቲን ስለፈረሰኞቹ የ2016 ካፍ ቻምፕየንስ ሊግ ማጣሪያ ድልድል ላይ ያላቸው አስተያየት ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያን አህጉራዊው ውድድር ላይ የሚወክለው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቅድመ ማጣሪያው የሲሸልስ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊን ይገጥማል፡፡ ይህንን ዙር ማለፍ ከቻለ የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊውን የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ክለብ የሆነውን ቲፒ ማዜምቤን የሚገጥም ይሆናል፡፡
የዩጋንዳ ብሄራዊ ብድንን በማሰልጠን ላይ የሚገኙት ሚቾ ቅዱስ ጊዮርጊስ በመጀመሪያው ዙር እምብዛም እንደማይፈተን እና ትልቁ ፈተና በመጀመሪያው ዙር ላይ እንደሆነ ያላቸውን ዕምነት ይናገራሉ፡፡ “በቅድመ ማጣሪያው ላይ ያለው ተጋጣሚ ለጊዮርጊስ የቀለለ ነው፡፡ ነገር ግን በመጀመሪው ዙር ማጣሪያ ቲፒ ማዜምቤ ለጊዮርጊስ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ማዜምቤን መግጠም ከባድ እንደሆነ ቢታወቅም እነሱ የተለዩ ፍጥረታት አይደሉም፡፡ ሰዎች ናቸው:: ስለዚህም ሊሸነፉ ይችላሉ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቲፒ ማዜምቤን ማሸነፍ ይችላል፡፡ በእግርኳስ ክለቦች ትልልቅ ውድድሮችን ካሸነፉ በኃላ ወደታች የመውረድ እና ተጋጣሚዎችን አቅልሎ የመመልከት አባዜዎች በስፋት ይታያሉ፡፡ ይህንን ተከትሎ ጊዮርጊሶች ለዚህ ትልቅ ፈተና መዘጋጀት አለባቸው፡፡” ሲሉ ሚቾ ሃሳባቸውን ያስረዳሉ፡፡
ቲፒ ማዜምቤ በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የአልጄሪያውን ዩኤስኤም አልጀርን አሸንፎ የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን በማንሳት አፍሪካን ጃፓን በመካሄድ ላይ ባለው የፊፋ የዓለም ክለቦች ዋንጫ ላይ ወክሎ 6ኛ ደረጃ ላይ ለመጨረስ ተገዷል፡፡
የፈረንሳይ ዜግነት ባላቸው የቀድሞ የማሊ ብሄራዊ ብድን አሰልጣኝ ፓትሪስ ካርትሮን የሚመራው የሉሙምባሺው ክለብ በዓለም ክለቦች ዋንጫ በጃፓኑ ሳንፌሬስ ሂሮሺማ እንዲሁም በሜክሲኮው ክለብ አሜሪካ ተሸንፎ ነው ስድስተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው፡፡
የአምስት ግዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊው ሚቾ ከተመሰረተ ሰማኒያኛ አመቱን በያዝነው ታህሳስ ወር እያከበረ ለሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፓርት ክለብ ያላቸውን መልካም ምኞት ገልፀዋል፡፡
“ቅዱስ ጊዮርጊስን የማየው እንደቤቴ ነው፡፡ በሃምሌ 1996 ክለቡን ለማሰልጠን ወደ ኢትዮጵያ ከመጣው ጀምሮ ለኔ ክለቡ የተለየ ቦታ በልቤ ውስጥ አለው፡፡ ክለቡን በማሰልጠኔ በጣም እኳራለው፡፡ የማይታመኑ አምስት ጣፋጭ አመታትን በጊዮርጊስ አሳልፊያለው፡፡ የጊዮርጊስ ክለብ እና ደጋፊዎቹን ላመሰግን እፈልጋለው፡፡ እንኳን ለ80ኛ አመት ልደታቹ አደረሳቹ፡፡ ለቀጣዩ ስራችሁ መልካሙን ሁሉ እመኛለሁ፡፡” በማለት ሚቾ ሃሳባቸውን አጠናቀዋል፡፡