የአሰልጣኞች አስተያየት | ኢትዮጵያ ቡና 0-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ላይ ከተጠበቁት ጨዋታዎች መካከል አንዱ የነበረው የሸገር ደርቢ ያለ ጎል ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

” ጊዮርጊሶች አፈግፍገው ስለነበር በራሳችን ሜዳ በርከት ያሉ ቅብብሎች ለማድረግ ተገደናል” ገዛኸኝ ከተማ (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለጨዋታው

“የዛሬው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ነጥቡን ፈልገን እንደመግባታችን ጥሩ ፉክክር የታየበት ነበር። ኳስን ተቆጣጥረን ለመጫወት ሞክረናል። በጉዳት ተጫዋቾች እንዳለመኖራቸው በአንድ አጥቂ ነበር የተጫወትነው። ቢሆንም እንደቡድን የተሻልን ነበርን፡፡”

በራሳቸው ሜዳ ብዙ ኳሶችን ስለመቀባበላቸው

“ከራሳችን ሜዳ መስርተን ለመውጣት ጥረት እያደረግን ነበር። በተቃራኒው ተጋጣሚያችን በጥልቀት በራሳቸው ሜዳ ክልል አፈግፍገው እየተከላከሉ ነበር። ስለዚህ እነሱን ስበን ለማውጣት በራሳችን ሜዳ በርከት ያሉ ቅብብሎች ለማድረግ ተገደናል። ቢሆንም አሁንም ወደ ፊት በመሄድ በኩል ችግሮች አሉብን፡፡”

” ቡናዎች አቻውን የፈለጉ ይመስል ነበር” ስቴዋርት ሃል (ቅዱስ ጊዮርጊስ)

ስለ ጨዋታው

“ጨዋታው በጥራት ደረጃው ከጠበቅኩት የተሻለ ነበር፤ አብዛኛዎቹ የማውቃቸው ደርቢዎች በከፍተኛ ውጥረት የተሞሉ በመሆናቸው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴው ሲጎዳ አስተውላለሁ፤ በዚህ ረገድ የተሻለ ነበር ጨዋታው፡፡ ቡድኔ ከሰሞኑ ጨዋታዎች አንፃር በተለይ በመጀመሪያው 10 እና 15 ደቂቃዎች የተሻለ መንቀሳቀስ አልቻልንም። በሂደት ግን ወደ ጨዋታው ቀስ በቀስ መግባት ችለናል፡፡በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ተንቀሳቅሰናል። ጨዋታውንም ለማሸነፍ ጥረት አድርገናል፡፡ ቡናዎች አቻውን የፈለጉ ይመስል ነበር፡፡ ፍፁም ቅጣት ምት ይገባን ነበር፤ ዳኛው ትልቅ ውሳኔ መወሰን ነበረበት። ትንንሽ ውሳኔዎችን በትክክል መወሰን በጣም ቀላል ነው። ነገርግን እንደ ዳኛ ትልቅ ዳኛ የሚያሰኘው እነዚህን አይነት ውሳኔዎች መስጠት ስትችል ነው፡፡”

ስለ ዋንጫ ጉዞ

“በቀጣይ ሁለት ጨዋታዎች በሜዳችን አሉን። እነሱን በማሸነፍ ወደ መስመራችን መመለስ ይኖርብናል፡፡ ስለ መቐለም ሆነ ፋሲል መጨነቅ የለብንም። ለጊዜው ማሰብ የሚገባን ስለራሳችን ብቻ ነው፡፡ ሁለት ነጥብ በመጣላችን ተበሳጭተናል። ነገር ግን በሁለተኛው አጋማሽ ያሳየነው እንቅስቃሴ ጨዋታውን ለማሸነፍ የሚያበቃን ነበር፡፡”


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡