በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 4ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አዳማ ከነማ መሪነቱን ሲያስጠብቅ ወላይታ ድቻ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተከታታይ ድላቸውን አስመዝግበዋል፡፡
አዲስ አበባ ስታድየም ላይ አርባምንጭ ከነማን ያስተናገደው መከላከያ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ እንግዳው ቡድን በትርታዬ ደመቀ የ23ኛ ደቂቃ ግብ መምራት ቢችልም ምንይሉ ወንድሙ በ83ኛው ደቂቃ መከላከያን ከሽንፈት የታደገች ግብ ከመረብ አሳርፏል፡፡
ቦዲቲ ላይ ወላይታ ድቻ ሀዋሳ ከነማን አስተናግዶ በፈቱዲን ጀማል ብቸኛ ግብ 1-0 በማሸነፍ 3ኛ ተከታታይ የፕሪሚየር ሊግ ድሉን አሳክቷል፡፡ ከፍተኛ የመሸናነፍ ፉክክር እና ውጥረት በነበረበት ጨዋታ የድቻው አማካይ አማኑኤል ተሾመ በ2 ቢጫ ከሜዳ ተወግዷል፡፡
አዳማ ላይ አዳማ ከነማ ደደቢትን 3-2 በማሸነፍ በአስደናቂ የሜዳ ሪኮርዱ ቀጥሏል፡፡ ዋንኛ ግብ አስቆጣሪው ሳሚ ሳኑሚን ሳይዝ ወደ ሜዳ የገባው ደደቢት በያሬድ ዝናቡ እና ዳዊት ፍቃዱ ሁለት ጊዜ የመምራት እድል ቢያገኝም የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የተሳካ የተጫዋች እና የታክቲክ ለውጥ ለቀይ ለባሾቹ 3 ነጥቦች አስኝቶላቸዋል፡፡ ተቀይሮ የገባው ቡልቻ ሹራም ሁለት ግቦችን በማስቆጠር የጨዋታውን መንፈስ ለውጦታል፡፡ አንጋፋው ታፈሰ ተስፋዬ ቀሪውን ግብ አስቆጥሯል፡፡
አዳማ ከነማ በሜዳው ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች በድል የተወጣ ሲሆን በ10 ነጥቦችም ሊጉን በመምራት ላይ ይገኛል፡፡

ሆሳእና ላይ ሀዲያ ሆሳእና ከ ሲዳማ ቡና አቻ ተለያይቶ በታሪኩ የመጀመርያውን ነጥብ ማሳካት ችሏል፡፡ አምና የጅማ አባ ቡና እና የጅማ ከነማን የፊት መስመር የመሩት ላኪ ባሪለዱም(ሲዳማ ቡና) እና አሸናፊ ይታየው (ሀዲያ ሆሳዕና) ግቦቹን አስቆጥረዋል፡፡
አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በተደረገው የእለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ኤሌክትሪክን በማሸነፍ ደረጃውን አሻሽሏል፡፡ ኤሌክትሪክ በፒተር ኑዋድኬ የ2ኛ ደቂቃ ግብ 1-0 ቢመራም ያቡን ዊልያም በ10ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ግብ ቡናን አቻ አድርጓል፡፡ ቡና በ26ኛው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት ቢያገኝም ጋቶች ፓኖም የመታው ኳስ በአሰግድ አክሊሉ ተመልሶበታል፡፡ (አሰግድ በሳምንቱ አጋማሽ የቀድሞው የአርሰናል ኮከብ ሬይ ፓርለር ከመታቸው ፍፁም ቅጣት ምቶች የመለሰ ብቸኛው ግብ ጠባቂ ነበር፡፡)
ትላንት በተደረጉ 2 ጨዋታዎች ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከነማን በናትናኤል ዘለቀ ግሩም ግብ 1-0 ሲያሸንፍ ንግድ ባንክ በአምሃ በለጠ ግብ ዳሽን ቢራን አሸንፏል፡፡
ሊጉን አዳማ ከነማ በ10 ነጥቦች ሲመራ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ በእኩል 9 ነጥቦች ይከተላሉ፡፡ የከፍተኛ ግብ አግቢነቱን ደግሞ ታፈሰ ተስፋዬ በ4 ግቦች ይመራል፡፡
ቀጣይ ጨዋታዎች
5ኛ ሳምንት
ሰኞ ታህሳስ 11 ቀን 2008
09፡00 – አርባምንጭ ከነማ ከ አዳማ ከነማ (አርባምንጭ)
09፡00 – ዳሽን ቢራ ከ መከላከያ (ጎንደር)
09፡00 – ሀዋሳ ከነማ ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ (ሀዋሳ)
09፡00 – ሲዳማ ቡና ከ ወላይታ ድቻ (ይርጋለም)
09፡00 – ድሬዳዋ ከነማ ከ ሀዲያ ሆሳእና (ድሬዳዋ)
11፡30 – ደደቢት ከ ኤሌክትሪክ (አአ)
ማክሰኞ ታህሳስ 12 ቀን 2008
11፡30 – ኢትዮጵያ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ (አአ)