የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 2-1 ድሬዳዋ ከተማ

በባህር ዳር ዓለማቀፍ ስታዲየም የተደረገው የባህር ዳር ከተማ እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ 2-1 በባለሜዳዎቹ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞች የሚከተለውን ብለዋል።

“ተጫዋቾቼ የሚከፈለውን መስዋትነት ከፍለዋል፣ በዚህም አሸንፈን ወጥተናል።” ጳውሎስ ጌታቸው (ባህር ዳር ከተማ)

ስለ ጨዋታው

በአጠቃላይ ተጫዋቾቼ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ከፍለዋል። ምክንያቱም ብዙ ነጥቦችን ጥለን ስለመጣን የዛሬው ጨዋታ እጅግ ያስፈልገን ነበር። እኔም ከዛ የነጥብ ማጣት ጉዞ እንዲወጡልኝ ፈለጌ ነበር። ይህም ደግሞ ተሳክቷል። በቀጣይ ያሉንን ጨዋታዎች አሸንፈን የዓመቱ ክስተት መሆናችንን እንቀጥላለን።

ስለ ተጫዋቾቻቸው ብቃት

ስለ ተጫዋቾቼ ከዚህም በፊት ብዬዋለው ያለ ቦታቸው እንኳን እየተጫወቱ ጥሩ አቋም ነው የሚያሳዩት። ለምሳሌ ዛሬ ግርማ ዲሳሳ ያለቦታው ነው የተሰልፈው፤ ነገር ግን ጥሩ ተንቀሳቅሷል። ከዚህ በኋላ አመቱ እያለቀ ስለሆነ የተጫዋቾች ጉዳት እና ድካም ይሆራል ስለዚህ ተጨዋቾቼ ቶሎ አገግመው እንዲመለሱ እየቀያየርን እናሰልፋቸዋለን።

ስለ ሁለተኛው አጋማሽ ብቃታቸው

ሁለት ግብ ካስቆጠርን በኋላ ወደ ግብ ክልላችን ሙሉ ለሙሉ ማፈግፈግ ፈልገን ሳይሆን ከዚህ በፊት የተፈጠሩ ነገሮችን ለመቀነስ ነው። ሁለት ለዜሮ እየመራን ሶስት ጎል የተቆጠረብ እና አቻ የተለያየንበትን ጨዋታ ላለመድገም ነው በደንብ መከላከል የፈለግነው። ይህ ደግሞ የሆነው ተጨዋቾቼ በራስ መተማመናቸውን በመጠኑ ስላጡ ነው።

ስለ ተጋጣሚ ቡድን

ተጋጣሚያች በመጀመሪያው ጨዋታ ድሬዳዋ ላይ አሸንፎን ነበረ። ነገር ግን ዛሬ በደጋፊያችን ፊት አሸንፈናቸዋል። በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ ቡድን ነው። ሲከላከሉም ሲያጠቁም በአንድነት ነው።

“በእንቅስቃሴ ደረጃ ጥሩ ብንሆንም ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ባለመጠቀማችን ተሸንፈናል።” ስምዖን ዓባይ (ድሬዳዋ ከተማ)

ስለ ጨዋታው

በእንቅስቃሴ ደረጃ በሙሉ 90 ደቂቃዉ የእኛ ቡድን የተሻለ ነበረ። ነገር ግን ጥሩ ተጫወትክም መጥፎ ሶስት ነጥብ ይዘህ መውጣት ካለቻልክ ዋጋ የለውም። ዛሬ ግን ተጨዋቾቼ ባሳዩት ብቃት ደስተኛ ነኝ። በአጠቃላይ ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ባለመጠቀመችን ተሸንፈናል።

ስለ ውጤቱ

በርግጠኝነት የምነግራችሁ ነገር የእኔ ቡድን ጠንካራ ነበረ። ጥሩ እንቅስቃሴም አይቼበታለሁ። የኢታሙኒ ገና በጊዜ ከሜዳ መውጣት የተወሰነ ጫና አሳድሮብናል ነገር ግን መጨረሻ ላይ ትንሽ ደቂቃ ብናገኝ ኖሮ ግብ እናስቆጥር ነበረ። እነደ አጠቃላይ ግን ተጭነን እንደመጫወታችን አንድ ነጥብ ይገባን ነበረ።

ስለ ተጋጣሚ ቡድን

ባህር ዳር ከበፊቱ በጣም ወርዶብኛል። የተሸነፍነውም በእነሱ ጥንካሬ ሳይሆን በእኛ ድክመት ነው። በተለይ የመጀመሪያው ጎል የተቆጠረበት መንገድ እኛ የፈጠርነው የትኩረት ማጣት ችግር ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡