ስሑል ሽረ ከኢትዮጵያ ዋንጫ ራሱን አግሏል

ስሑል ሽረ በፕሪምየር ሊጉ ላይ ትኩረት ለማድረግ ስላሰብኩ ራሴን ከኢትዮጵያ ዋንጫ (ጥሎ ማለፍ) አግልያለሁ ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ ከከፍተኛ ሊግ ካደጉ ክለቦች መካከል አንዱ የሆነው ስሑል ሽረ ካደረጋቸው 24 ጨዋታዎች 22 ነጥቦችን ሰብስቦ ከግርጌው ከፍ ብሎ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ክለቡ ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ባይችልም በሁለተኛው ዙር በተሻለ የውጤት ጉዞ ላይ ይገኛል፡፡ ይህንን ውጤት አስቀጥሎ ለመዝለቅ እና በሊጉ ለመቆየት ፕሪምየር ሊጉ ላይ ትኩረት ሰጥቼ መወዳደርን ስለምፈልግ ከኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር ራሴን አግልያለሁ በማለት ራሱን ከፉክክሩ ውጪ ማድረጉን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ መረጃውን አግኝታለች፡፡ ይህን ተከትሎም ሲዳማ ቡናን በመርታት የኢትዮጵያ ዋንጫን የመጀመሪያው ዙር ያለፈው ክለቡ በነገው ዕለት ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም ሊያደርገው የነበረው ጨዋታ በቡና አሸናፊነት በፎርፌ ተጠናቆ ቡና በቀጥታ ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚያልፍ ይሆናል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና በመጀመርያ ዙር ማጣርያ ከደደቢት ጋር ተደልድሎ የነበረ ቢሆንም ሰማያዊዎቹ ራሳቸውን ከውድድሩ በማግለላቸው ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፎ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ሽረ ራሱን በማግለሉ ጨዋታ ሳያደርግ ወደ ግማሽ ፍፃሜው መሸጋገር ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡