የድሬዳዋ ከተማው አጥቂ ከሀገሩ ጋር ወደ አፍሪካ ዋንጫው ያመራል


ናሚቢያዊው የድሬዳዋ ከተማ አጥቂ ኢታሙና ኬሙይኔ ወደ አፍሪካ ዋንጫው እንደሚያመራ ያረጋገጠ ሁለተኛው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተጫዋች ሆኗል።

በዓመቱ መጀመርያ ቱራ ማጂክን ለቆ ብርቱካናማዎቹን በመቀላቀል ጥሩ ዓመት ያሳለፈው ይህ ናሚቢያዊ አጥቂ በርካታ የአጥቂ አማራጮች የነበራቸው አሰልጣኝ ሪካርዶ ማኔቲን በማሳመን ሃገሩን ለመወከል ወደ መጨረሻው ዝርዝር ተካቷል። ባለፉት ሳምንታት ጉዳት ላይ የነበረው አጥቂው በዚ ሰዓት ሙሉ ጤንነት ላይ ሲገኝ ለቋሚ ተሰላፊነት ከኢስማዒልያው አጥቂ ቤንሰን ሺሎንጎ እና ሌሎች ሁለት ተጫዋቾች ጋር ይፎካከራል።

በዱባይ ፖሊስ ስታድየም ዝግጅታቸው እያደረጉ የሚገኙት ናሚቢያዎች ትላንት በአቋም መለኪያ ጨዋታ ትልቋ ጋና 1-0 ማሸነፋቸው ይታወሳል።

ባለፈው ሳምንት የቅዱስ ጊዮርጊሱ ኬንያዊ ግብጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ በግብፁ አፍሪካ ዋንጫ ሃገሩን እንደሚወክል መረጋገጡ ሲታወስ ኡታሙና ኬይሙኔም ከግብ ጠባቂው ቀጥሎ ከኢትዮጵያ ክለቦች ወደ አፍሪካ ዋንጫው የሚያመራ ሁለተኛ ተጫዋች ሆኗል።

ዩጋንዳውያኑ ሮበርት ኦዶንካራ እና ክሪዚስቶም ንታንቢ እንዲሁም ብሩንዳዊ ሑሴን ሻባኒ ሌሎች ወደ ግብፅ ለማምራት የመጨረሻውን ምርጫ የሚጠባበቁ ተጫዋቾች ናቸው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡