የአፍሪካ ዋንጫ ዳሰሳ | ምድብ አንድ

የአፍሪካ ዋንጫ በግብፅ አስተናጋጅነት ከሰኔ 14 እስከ ሐምሌ 14 ይካሄዳል። የጊዜ እና የተሳታፊ ቁጥር ለውጥ ከተደረገ በኋላ የሚከናወነው የመጀመርያ ውድድርን አስመልክቶ ምድቦቹን በተናጠል እንዳስሳለን። የዛሬው መሰናዶም ምድብ ሀ ላይ ያተኩራል።

አዘጋጇ ግብፅን ጨምሮ ዩጋንዳ፣ ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ እና ዚምባብዌን የያዘው ይሄ ምድብ በማጣርያው ጉዞ ድንቅ አቋም አሳይተው በመሪነት ያጠናቀቁት ሁለት ቡድኖች እና በደጋፊያቸው ፊት የሚጫወቱት ፈርዖኖች የሚያገናኝ እንደመሆኑ ጥሩ እና ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይባቸዋል ተብለው ከሚገመቱት ምድቦች አንዱ ያደርገዋል።

🇪🇬 ግብፅ

የተሳትፎ ብዛት – 24

ምርጥ ውጤት
– 7 ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ (1957፤ 59፣ 86፣ 98, 06, 08, 10)

በምድብ ‘J ‘ከመሪዋ ቱኒዚያ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብላ በሁለተኛነት ምድቡን ያጠናቀቀችው አዘጋጇ ግብፅ ምንም እንኳ ከሌሎች አገሮች አንፃር ሲታይ በዚህ ዓመት ከክለባቸው ጋር ጥሩ ጊዜ ያሳለፉት ኮከብ ተጫዋቾች በብዛት ባይኖሯትም በደጋፊዎቿ ፊት መጫወቷ እና በሊቨርፑል ድንቅ ዓመት ያሳለፈው እና በማጣርያ ጨዋታዎች አራት ግቦች ያስቆጠረው ኮከቡ መሐመድ ሳላህ መያዟ ግን ቀላል ግምት አይሰጣትም።

በሃገራቸው በነበረው የፖለቲካዊ ቀውስ ምክንያት ለበርካታ ዓመታት ከነገሱበት ውድድር ርቀው የነበሩት ፈርዖኖች ከረጅም ግዜ በኃላ
በተመለሱበት የባለፈው አፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ደርሰው ያጡትን ዋንጫ አልመው ወደ ውድድሩ እንደሚገቡ እሙን ነው። ከዚህ በተጨማሪ ፈርዖኖቹ በቀድሞ አሰልጣኛቸው ሄክቶር ኩፐር ከተከተሉት እጅግ አሰልቺ አጨዋወት ተላቀው ወደሚታወቁበት አጨዋወት ይመለሳሉ ተብሎ ሲጠበቅ በመሐመድ ሳላህ እና ሙሐመድ ትሬዜጌ ትልቅ ተስፋ ጥለው ወደ ውድድሩ ይገባሉ።

ከደቡብ አፍሪካ ቀጥለው ብዙ ተጫዋቾች ከሃገር ውስጥ ሊግ ያስመረጡት ፈርዖኖቹ ከዘጠኝ ተጫዋቾች በስተቀር አስራ አራት ተጫዋቾች ከሃገር ውስጥ ቡድኖቻቸው አካተዋል። ሜክሲካዊ አሰልጣኝ ዣቭየር አግዌሬ ዋንጫው በግብፅ ከማስቀረትም በተጨማሪ ቡድኑን በደጋፊው ካልተወደደው አሰልቺው አጨዋወት ሙሉ በሙሉ የማስወጣት ፈተናም ይጠብቃቸዋል።

🇺🇬 ዩጋንዳ

የተሳትፎ ብዛት – 7

ምርጥ ውጤት – የፍፃሜ ተፋላሚ (1978)

በምድቧ ብቻ ሳይሆን በውድድሩ ክስተት ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት ቡድኖች አንዷ ዩጋንዳ ናት።
ባለፉት አምስት ዓመታት በወጥነት ምርጥ ቡድን የሰሩት ዩጋንዳዎች በውድድሩ ልምድ ባይኖራቸውም በማጣርያው ላይ በባሳዩት ብቃት ተጠባቂ ያደርጋቸዋል። ምድብ ‘ L ‘ በ አስራ ሶስት ነጥብ በበላይነት የጨረሱት የሴባስትያን ደሳብሬ ስብስብ የወቅቱ የአፍሪካ ኮከብ ግብጠባቂ ዴኒስ ኦኔያንጎ እና ግብ አስቆጣርያቸው ፋሩክ ሚያ ከቡድኑ የሚጠበቁት ተጫዋቾች ናቸው።

ከሰርብያዊው አሰልጣኝ ሰርጅዮቪች ሚቾ የተረከቡትን ውጤታማ ቡድን ማስቀጠል የቻሉት ሰባስትያን ደሳብር የቀድሞ አሰልጣኙ ከሁለት ዓመት በፊት ያላሳካውን ስኬት ለመቀየር ተስፋ ሰንቀው ወደ ግብፅ ይበራሉ። ቡድኑ ምንም እንኳ አስፈሪ የመከላከል ጥምረት ቢኖረውም ግብ በማስቆጠር እና ንፁህ የግብ ዕድሎች በመፍጠር ረገድ ያለው ክፍተት ግን የቡድኑ ትልቅ ስጋት ነው።
በተለይም ግብ ማስቆጠር ላይ ያለው ችግር ስር የሰደደ ነው። ከዚ በተጨማሪም ቡድኑ በጥቂት ተጫዋቾች ብቻ የተንጠለጠለ የግብ ማግባት ኃላፊነት ያለው ቡድን በመሆኑ ሌላው የሚነሳ መጥፎ ጎን ነው በዚህም በማጣሪያ ጨዋታዎቹ በፋሩክ ሚያ ፣ ኢማኑኤል ኦኩዊ ፣ ፓትሪክ ካዱ እና ጆፍሬይ ሰሩንኩማ አማካኝነት ብቻ ነበር ግብ ማግኘት የቻሉት።

ዩጋንዳዎች በመጨረሻው ምርጫ የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ ክሪዚስቶም ንታንቢን ጨምሮ ቻርለስ ሉክዋጎ፣ ሳዳም ጁማና አሌክሲስ ባካ ጥለው ነበር ወደዚ ውድድር የመጡት።

🇨🇩 ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ

የተሳትፎ ብዛት – 28

ምርጥ ውጤት – ሁለት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ (1968፣ 1974)

ሌላ በምድቡ ከሚገኙት ቡድኖች ጥሩ ግምት የሚሰጣቸው በፍሎረን ኢቤንጌ የሚመሩት ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ሲሆኑ በማጣሪያ በምድብ ‘G’ ከዚምባብዌ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብለው በሁለተኛነት ነበር ያጠናቀቁት። ከሀገሪቱ ቡድኖች እና በአውሮፓ ዝቅተኛ ሊጎች ከሚገኙ ተጫዋቾች ቡድናቸው ያዋቀሩት ኮንጎዎች በተጫዋቾች ደረጃ በዓመቱ ጥሩ ጊዜ ያሳለፉት በርካታ ተጫዋቾች ባይኖራቸውም በአፍሪካ ውድድሮች ከቲፒ ማዜምቤና ኤኤስ ቪታ ጋር በርካታ ልምድ ያካበቱ ተጫዋቾች መያዛቸው በምድቡ ቀላል ግምት እንዳይሰጣቸው ያደርጋቸዋል።

ከዚህ ውጭ በማጣርያው ላይ ሦስት ግቦች ያስቆጠረውና ከቻይናው ክለብ ቤጂንግ ጎአን በጣም ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ የሚገኘው ኮከባቸው ሴድሪች ባካምቡ ፣ ያኒክ ቦላሴ እንዲሁም የዌስትሃሙ አርተር ማሱዋኩን በቡድናቸው ማካተታቸው በውድድሩ የተሻለ ጉዞ እንድያደርጉ ያግዛቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በስፔኗ ማርቤላ ዝግጅታቸው በማድረግ የቆዩት ኮንጎዎች እንደ ዩጋንዳ ሁሉ በማጣርያው ግብ ለማስቆጠር ሲቸገሩ ተዋውሏል።

🇿🇼 ዚምባብዌ

የተሳትፎ ብዛት – 3

ምርጥ ውጤት – የምድብ ጨዋታ

እንደ ዩጋንዳ ሁሉ በውድድሩ ላይ ከሚጠበቁት ቡድኖች አንዷ የሆነችው ዚምባብዌ ሳትገመት ነበር ሁለቱን ኮንጎዎች እና ላይቤርያን አስከትላ ምድቡን በ11 ነጥቦች በበላይነት ያጠናቀቀችው። በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ በሦስት ውድድሮች ብቻ በመካፈል ብዙ የመሳተፍ ክብረ ወሰን የሌላት ዚምባብዌ በአመዛኙ ቡድኗ ከአፍሪካ ሊጎች ከተወጣጡ ተጫዋቾች የገነባች ብትሆንም በማጣርያው ባሳየችው ብቃት ቀላል ግምት አይሰጣትም።

ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በማጣርያው ላይ አምስት ግቦች ያስቆጠረው የቀድሞ የሆፈንሄይም እና ኦግስበርግ ፤ አሁን በአንደርሌክት የሚጫወተው ናውሌጅ ሞሶናን መያዙ ቀላል ግምት አይሰጠውም።

በምድቡ ተጠባቂ ጨዋታ፡ ግብፅ ከ ዩጋንዳ

ምድቡ እንደሌሎች ምድቦች ከወዲሁ በበርካቶች በጣም ተጠባቂ ጨዋታ ባይኖረውም አዘጋጅዋ ግብፅ እና የወቅቱ ተወዳሽ አገር ዩጋንዳ የሚያገናኘው ጨዋታ የምድቡ ተጠባቂ ጨዋታ ነው። ድንቅ የማጥቃት ክፍል እና ጥሩ የመከላከል ክፍል ያላቸው ሁለት ቡድኖች የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ ኮከቡ መሐመድ ሳላህ እና የወቅቱ የአፍሪካ ምርጥ ግብ ጠባቂ ዴኒስ ኦኔያንጎን ያገናኛል።

ከምድቡ የሚጠበቅ ኮከብ ተጫዋች – መሐመድ ሳላህ

ከምድቡ ብቻ ሳይሆን በውድድሩም ይደምቃል ተብሎ የሚጠበቀው መሐመድ ሳላህ ነው። ከሊቨርፑል ጋር ሁለተኛ ድንቅ ዓመት ያሳለፈውና ሁለት ተከታታይ ዓመታት የዓለማችን ትልቁ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው መሐመድ ሳላህ ግብፅን ከ11 ዓመታት በኋላ ለዋንጫ እንድትገመት እያደረጋት ይገኛል።

የምድቡ ጨዋታዎች

ዓርብ ሰኔ 14 ቀን 2011
ግብፅ ከ ዚምባብዜ (4:00፤ ካይሮ)

ቅዳሜ ሰኔ 15 ቀን 2011
ዲሪ ኮንጎ ከ ዩጋንዳ (10:30፤ ካይሮ)

ረቡዕ ሐምሌ 19
ዩጋንዳ ከ ዚምባብዌ (1:00፤ ካይሮ)
ግብፅ ከ ዲሪ ኮንጎ (3:00፤ ካይሮ)

እሁድ ሰኔ 23

ዩጋንዳ ከ ግብፅ (3:00፤ ካይሮ)
ዚምባብዌ ከ ዲሪ ኮንጎ (3:00፤ 30 ጁን)

©የስም ዝርዝር ምስሎች ከካፍ የተወሰዱ ናቸው