ሪፖርት| መቐለ በቻምፒዮንነት ሩጫው ሲቀጥል መከላከያ ሊጉን ተሰናብቷል

በ29ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መርሐ ግብር መቐለ 70 እንደርታ መከላከያን 2ለ1 በመርታት ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋር በእኩል ነጥብ ወደ መጨረሻው ሳምንት አምርቷል። መከላከያ ደግሞ ከ14 ዓመታት የፕሪምየር ሊግ ቆይታ በኃላ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱ ተረጋግጧል።

ጨዋታ ሊጀመር የተወሰኑ ሰዓታት እስኪቀሩ ድረስ በተያዘለት መርሐግብር የመካሄዱ ነገር ሳይለይለት ቢቆይም በስተመጨረሻም ጨዋታው በተያዘለት መርሃግብር ሊካሄድ ችሏል፡፡ ሁለቱም ቡድኖች በአመዛኙ በውድድር ዘመኑ የጠቀሙባቸው የነበሩ ተጫዋቾች በዛሬው ጨዋታ የተጠቀሙ ሲሆን በጎልህ ሊጠቀስ የሚችለው ለውጥ በመቐለዎች በኩል የቡድኑ ተመራጭ የግብ ዘብ የሆነው ፊሊፕ ኦቮኖ በሶፎንያስ ሰይፈ ተተክቶ ጨዋታውን መጀመሩ ነው።

በመጀመሪያው አጋማሽ መከላከያዎች በተሻለ የማሸነፍ ፍላጎት በፍጥነት ወደ ጎል ለመድረስ ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም በተደራጀ መልኩ ለግብ ክልላቸው ቀረብ ብለው ሲከላከሉ የነበሩት የመቐለ ተጫዋቾችን አልፈው የጠራ የግብ እድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ መቐለዎች ደግሞ በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች በመከላከያዎች የግራ መስመር በኩል በሁለት አጋጣሚዎች ያሬድ ብርሃኑ ከተከላካዮች ጀርባ የተጣሉትን ኳሶች በሁለቱም አጋጣሚ በደካማ የውሳኔ አሰጣጥ የተነሳ ሳይጠቀምባቸው ቀረ እንጂ ጥሩ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡ በመከላከያዎች በኩል በ30ኛው ደቂቃ ላይ ከቋመ ኳስ የተሻማውን ኳስ ሶፎንያስ ሲተፋ በቅርብ ርቀት የነበረው ዳዊት እስጢፋኖስ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጪ የወጣችበት ኳስ አስቆጭ ሙከራ ነበረች፡፡

መከላከል ላይ ትኩረት በማድረግ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት አስበው የገቡ የሚመስሉት መቀለዎች በ36ኛውና በ38ኛው ደቂቃ ለመሀል ሜዳ ቀርበው ሲከላከከሉ ከነበሩት የመከላከያ ተከላካዮች ጀርባ በግሩም የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በአማኑኤል ገ/ሚካኤል እንዲሁም ኦሲ ማውሊ አማካኝነት ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል፡፡

እነዚህ ሁለት ግቦች በመነቃቃት ላይ የነበሩትን የመከላከያ ተጫዋቾች ተነሳሽነት በእጅጉ የጎዱ ነበሩ፤ ከግቧ መቆጠር በኃላ የመከላከያ ተጫዋቾች ፍፁም ባለመረጋጋት ውስጥ ሆነው ነበር የመጀመሪያ አጋማሹን ያጠናቀቁት፡፡

በመጀመሪያ አጋማሽ መገባደጃ ላይ የመቐለው የቀኝ መስመር ተከላካይ ስዮም ተስፋዬ ፍሬው ሰለሞን ላይ በሰራው ጥፋት እንዲሁም ቀጥሎ ባሳየው ያልተገባ ባህሪ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ሊወገድ ችሏል፡፡

ከመልበሻ ቤት መልስ መከላከያዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ጨዋታውን በተሻለ መልኩ ነበር መጀመር የቻሉት ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ተመስገን ገ/ኪዳንና ፍፁም ገ/ማርያምን አስወጥተው በግዙፎቹ ፍቃዱ ዓለሙና አቅሌሲያስ ግርማ በመተካት ከመጀመሪያው አጋማሽ በተለየ ቡድኑ ከሚታወቅበት ኳስን መሠረት ካደረገ አጨዋወት በተለየ በቀጥተኛ አጨዋወት ነገሮችን ለመቀየር ታሳቢ ያደረገን ቅያሬ በማድረግ ነበር ጨዋታውን የጀመሩት፡፡ ጦረኞቹ ምንም እንኳን ሁለት በተክለ ሰውነታቸው የተሻሉ አጥቂዎችን ፊት ላይ ቢይዙም ኳሶችን በቀጥታ ከማድረስ ይልቅ አላስፈላጊ ቅብብሎች እንዲሁም ደካማ የኳስን የማሻማት ሂደት ቅያሬዎቹ ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ በ49ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ፍቃዱ ያሸነፈለትን የመጀመሪያ ኳስ ተጠቅሞ አቅሌሲያስ ግርማ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የላካት ኳስ የግቡን አግዳሚ ለትማ ወደ ውጭ የወጣችበት ኳስም አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች፡፡

መከላከያዎች ፍፁም የበላይ በነበሩበት በሁለተኛው አጋማሽ መከላከያዎች ጨዋታውን ለመቀየር የተቻላቸውን ጥረት አድርገዋል፤ ቴዎድሮስ ታፈሰ በ52ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት እንዲሁም በ55ኛው ላይ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ያደረጋቸውን ግሩም ሙከራ ሶፎንያስ ሰይፈ ሊያድንበት ችሏል፡፡

መቐለዎች በሥዩም ተስፋዬ ቀይ ካርድ ጋር ተዳምሮ በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ በቀረበ ርቀት የተደረደሩ ሁለት ባለ አራት ተጫዋቾች የመከላከል መስመርን በመስራት በእጃቸው የገባውን ውጤት ለማስጠበቅ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው የመቀለ ተጫዋቾች ኳስን መልሰው በሚያገኙበት ወቅት ያለ አላማ ኳሱን እጅግ በበርካታ አጋጣሚዎች ሲያሻግሩ ተስተውሏል፡፡

በ82ኛው ደቂቃ ላይ መከላከያዎች ከመቐለ የግብ ክልል በቅርብ ርቀት ያገኙትን የቅጣት ምት ቴዎድሮስ ታፈሰ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቢልክም ኳሷ የግቡን አግዳሚ ለትማ ወደ ውጭ ወጥታለች፡፡ በ90ኛው ደቂቃ ላይ በሀይሉ ግርማ ከቡድን አጋሮቹ የደረሰውን ኳስ በግሩም ሁኔታ አክርሮ በማስቆጠር የቡድኑን ተስፋ ቢያለመልምም በተጨመረው ሦስት ደቂቃ ውስጥ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ባለመቻላቸው ጨዋታው በመቐለ የ2ለ1 የበላይነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

በዚህ ውጤት መሠረት መቐለ አሁንም በፋሲል ከነማ በግብ ልዩነነት ተበልጦ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ የዋንጫው ትንቅንቅ በመጪው በ30ኛ ሳምንት እልባት የሚያገኝ ይሆናል። በተቃራኒው መከላከያ ደደቢት እና ደቡብ ፖሊስን ተከትሎ ወደ ከፍተኛ ሊግ የወረደ ሦስተኛው ቡድን መሆኑን አረጋግጧል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡