“በእግር ኳስ ስኬት በዋንጫ አይመዘንም፤ በተከታታይ ጥሩ ውጤት ማምጣቴ ግን ትልቅ ደስታ ፈጥሮልኛል” ገብረመድህን ኃይሌ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2011 የውድድር ዘመን ባሳለፍነው እሁድ ፍፃሜውን ሲያገኝ መቐለ 70 እንደርታ ዋንጫውን ማንሳቱ ይታወሳል። ዓምና ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ሊጉን ያሸነፉት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌም በተከታታይ ዓመት ከሁለት የተለያዩ ቡድኖች ጋር ዋንጫውን በማሸነፍ ባለታሪክ ሆነዋል። አሰልጣኙ ስለ ድሉ እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ዓመቱ እንዴት ነበር?

ዓመቱ በጣም አስቸጋሪ አሰልቺ እና ፈታኝ ነበር።
በሀገራችን ባለው ነባራዊ የፖለቲካ ትኩሳት የፈጠረው ነገር አለ፤ በየአከባቢው የሚገጥሙን ችግሮች ነበሩ። ውድድሩ ትዕግስት የሚጠይቅና በጣም ከባድ ዓመት ነበር።

በተከታታይ የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ችለሃል። የድሉ ሚስጠር ምንድነው ?

የተለየ ሚስጠር የለውም፤ የስራ ውጤት ነው።
ለስራህ እና ለሞያህ ክብር ሰጥተህ መስራት ነው ዋናው ነገር። እኔ ለስራዬ ትልቅ ትኩረት ሰጥቼ ነው የምሰራው። በስራዬ አልደራደርም፤ ሁሉም ነገር በሰዓቱ ነው የማደርገው። በእያንዳንዱ ስራዬ ደቂቃም ማሳለፍ አልፈልግም። በእያንዳንዱ ነገር ሰዓቴ ጠብቄ ስለማከናውን የስራ ፍላጎቴም በጣም ትልቅ ነው። ከዚ በኃላም በጣም ብዙ ስራ እሰራለው ብዬ አምናለሁ።

በተከታታይ ዓመት የሊጉን ክብር ያገኘ አሰልጣኝ ሆነሃል እና በግልህ ምን ስሜት ፈጠረብህ ?

እንደ ባለሙያ በጣም ደስ ብሎኛል። ከዚ በላይም እሰራለው ብዬ ነው የማምነው ክብሩ በፕሪምየር ሊግ ከለካነው ነው እንጂ በኢትዮጵያ ዋንጫም እንዲ ተከታታይ ጥሩ ክብረ ወሰን አለኝ። በዋንጫ የሚለካ ከሆነ ጥሩ ታሪክ ነው ያለኝ። ግን እሱ አይደለም መለኪያ መሆን ያለበት። ቡድንህ እንደ ቡድን ጥሩ መሰረት አስይዘህ መስራት፣ በወጣቶች ላይም መስራት እና ዘላቂነት ያለው ጥሩ ቡድን መስራት ነው በእግር ኳስ ትልቁ ስኬት አድርጌ የማስበው። እኔ ደግሞ አዳዲስ ተጫዋቾች በማውጣት ችግር የለብኝም። ከዚ በፊት ብዙ ጊዜ በሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች ከቡድኔ ውስጥ ነበሩ። በችግሮቻቸው ሰርቼ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ጠለቅ ብዬ ነው የምገባው። በእግር ኳስ ስኬት በዋንጫ አይመዘንም። በተከታታይ ጥሩ ውጤት ማምጣቴ ግን ትልቅ ደስታ ፈጥሮልኛል።

በሁለተኛው ውድድር ዘመን አጋማሽ መዳከሞች ነበሩ። እንደ ምክንያት ምን ሊጠቀስ ይችላል?

መዳከሞቹ በርካታ ችግሮች የፈጠሯቸው ናቸው።
በሁለተኛው ዙር የተፈጠሩብን በርካታ ጫናዎች ነበሩ። በተለይም አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ሁሉም ቡድኖች እኛ ላይ የተለየ ትኩረት እንዲያደርጉ አድርገዋል። ገና ሁለተኛው ዙር በአምስት ነጥብ ልዩነት ስናጠናቅቅ የተለዩ መገናኛ ብዙሃን እዚ ሄደው ማሸነፍ አይችሉም እዛ ሄደው ማሸነፍ አይችሉም። ብለው የስነ ልቦና ጫና ፈጥረውብናል። ሌሎች ቡድኖች ለኛ የተለየ ዝግጅት እንዲደርጉ በመደረጉ በሄድንበት ብዙ ፈተናዎች ገጥሞናል። ሌሎች ውጫዊ ተፅዕኖዎች ተጨምረውበት። ይሄ የፈጠረው መዳከሞች ታይተውብን ነበር። የስነ ልቦናው ጫና የፈጠረው ነገርም ነበር። ህጉ በሚፈቅደው ነገር ከነዚህ ነገሮች ነፃ ሆነው ቢጫወቱ ሊጉ ከመጠናቀቁ ከሦስት አራት ጨዋታዎች በፊት ሊጉን ማሸነፋችን እናረጋግጥ ነበር።

በቻምፒየንስ ሊጉ ምን አይነት ውጤት ለማምጣት ነው ያቀዳችሁት?

ውድድሩ በቀጣይ ወር እንደሚጀመር በቅርብ ግዜ ነው ያወቅነው። ቀድመን ብናውቅ በተወሰነ መልኩ ለመስራት እና ነገሮች ለማስተካከል እንችል ነበር በተወሰነ መልኩ ለውድድሩ ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ፤ እንደ አጋጣሚ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫውን ካነሳነው ብለን ቀድመን የምናዘጋጀው አንዳንድ ነገር ይኖር ነበር። እሱም ብዙም በቂ ባይሆንም። በቅርብ ነው ውድድሩ መቃረቡ የሰማነው ብዙ ስራዎች አሉብን። በአጭር ግዜ ውስጥ ለቡድኑ ተጫዋቾች መመልመል አለ ፣ ውል ማራዘም አለ፤ ሌሎች ስራዎችም አሉብን።

ፈታኝ ነው በጣም፤ ምንም እንኳ የነበረውን ችግር አልፈን ቻምፒዮን መሆናችን በጣም ትልቅ ነገር ቢሆንም አሁንም ከፊት ለፊታችን ብዙ ነገር ይጠብቀናል። እንደ ቡድናችን ሁሉም ነገር አሟልተን በውድድሩ የሚቻለንን እናደርጋለን።
ሁሉም ነገር በግዜ ካስተካከልን ጥሩ ጉዞ እናደርጋለን። የካፍ የውድድር ስነ-ስርዓት ከዚ ቀደም ከነበረው ተቀይሯል። በቻምፒየንስ ሊጉ ሁለተኛው ዙር መሰናበት በኃላም በኮንፌደሬሽን ዋንጫ የመሳተፍ ዕድልም ስላለ ደጋፊያችን ቡድኑ በትላልቅ ውድድሮች የማየት ዕድልም ስላለው ቡድናችን የበለጠ የሚነሳሳበት ዕድልም ስላለ ውድድሩን በደምብ እንጠቀምበታለን።

ቡድኑ አጭር የዕረፍት እና የዝግጅት ወቅት ነው ያለው። በዚ አጭር ግዜ ቡድንህ እንዴት ለማዘጋጀት ነው ያሰብከው?

በተቻለ መጠን ለማመቻቸት እንሞክራለን። ተጫዋቾቻችን ዓመቱ ሙሉ ለፍተዋል ደክመዋል ቢያንስ የአንድ ወር ዕረፍት መስጠት ይገባን ነበር። አንድ ወር መስጠት አንችልም እስከ ውድድሩ ጅማሬ ያለው ግዜ ራሱ አንድ ወር ነው ፤ ከዛ በተጨማሪም አሁን ውድድር ላይ ነው ያለነው አሁን የተወሰነ ግዜ ዕረፍት ሰጥተን ከዛ ቶሎ ወደ ቅድመ ውድድር ዝግጅት ለመግባት ነው ያሰብነው። ይሄ በቀጣይ አሉታዊ ተፅዕኖው ቀላል አይሆንም ምክንያቱም ተጫዋቾች ወደ ውድድር ከመግባታቸው በፊት በቂ ዕረፍት ካላገኙ ድካሙ ከአቅማቸው በላይ ነው የሚሆነው። ይሄ ነገር እንዴት መፍታት እንችላለን ለሚለው ደግሞ በቀጣይ ግዜ የምናየው ነው የሚሆነው።

በኢትዮጵያ ዋንጫ መሳተፍ መቀጠላቹ በቀጣይ የውድድር ዓመት ጉዟቹ ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም ከድካም አንፃር?

ከመከላከያ ጨዋታ በፊት ለማግለልም ግዜ አልነበረንም። ከጨዋታው አንድ ቀን ሁለት ቀን በፊት አንሳተፍም ማለት አልፈለግነውም። በሌላ በኩል የመጫወት ዕድል ያልተሰጣቸው ተጫዋቾች የምናይበት ዕድልም ስለሆነ እሱን ለመጠቀም አስበንም ነው። ዋንጫው ይህን ያክል አስፈላግያችን እንዳልሆነ መታወቅ አለበት።

ባላቹህ አጭር ግዜ ወደ ዝውውሩ ሂደት መቼ ለመግባት አስባቹሃል ?

በተለያዩ መንገዶች ተጫዋቾች ለማዘዋወር እንቅስቃሴዎች ጀምረናል። ግን እንደሚታወቀው እኛ ሃገር ያለው ችግር የዝውውሩ ሂደት ይጓትታል።
መጓተቶቹ ቶሎ ወደፈለግክበት መስመር እንዳትገባ ያደርጉሃል ሌላው የቡድናችን በጀትም ቶሎ ማወቅ አለብን ፤ ወደ ዝውውሩ ቶሎ እንገባለን።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡