ወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ለመቅጠር የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቷል

ከአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በኋላ በአሰልጣኝ ቅጥር ዙርያ መረጋጋት ያልቻለው ወላይታ ድቻ አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር የቅጥር ማስታወቂያ አውጥቷል።

ወላይታ ድቻን በዘንድሮ የውድድር ዓመት አንደኛው ዙር ከተጠናቀቀ በኋላ ክለቡ ባወጣው የአሰልጣኝነት ቅጥር አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ተወዳድረው መቀጠራቸው ይታወቃል። እስከ ዓመቱ ፍፃሜ ድረስ ከቡድኑ ጋር ስኬታማ ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከወላይታ ድቻ ጋር ውል በማራዘም ይቆያሉ ተብሎ ሲጠበቅ ሳይታሰብ በቅርቡ ወደ ቀድሞ ክለባቸው አዳማ ከተማ መመለሳቸው ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ ወላይታ ድቻ የ2012 የውድድር ዘመን አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር ዛሬ የአሰልጣኞች ቅጥር ማስታወቂያ አውጥቷል። መስፈርቶቹም የሚከተሉት ናቸው፡-

* የካፍ የc ላይሰንስ ያለው
* ከአንደኛ ሊግ እስከ ፕሪምየር ሊግ ሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ ያሰለጠነ
* የሥነ ምግባር ችግር የሌለበት፤ ታማኝ፣ የስፖርት ክለቡን ደንብ እና መመርያ አክብሮ የሚሰራ
* አሁን ያለውን የቡድኑን ወቅታዊ አቋም የሚያውቅ እና ሰርቶ የተሻለ ውጤታማ የሚሆን።
* አቅም ያለቸውን ተጫዋቾች መምረጥ የሚችል።
* ደሞዝና ጥቅማጥቅም በስምምነት

አመልካቾች ማመልከቻቸውን በመያዝ ከሐምሌ 15–19 ቀን እንዲመዘገቡ ክለቡ ጥሪ አድርጓል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡