ኬሲሲኤ የሴካፋ ካጋሜ ካፕ አሸናፊ ሆኗል

ላለፉት ሦስት ሳምንታት በሩዋንዳ አዘጋጅነት ሲካሄድ የቆየው የሴካፋ ካጋሜ ዋንጫ በኬሲሲኤ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

የዞኑ ትላልቅ ቡድኖች ትኩረት የተነፈገውና በሩዋንዳው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ስፖንሰርነት የተካሄደው የሴካፋ ካጋሜ ዋንጫ በትናንትናው ዕለት ፍፃሜው ሲያገኝ በፍፃሜው የዩጋንዳው ኬሲሲኤ እና የዓምናው የውድድሩ ባለ ድል የታንዛኒያው አዛም ያገናኝ ሲሆን ኬሲሲኤዎች በሁለተኛው አጋማሽ በመስመር ተከላካዩ ሙሲጣፋ አማካኝነት ባስቆጠሯት ብቸኛ ግብ ጨዋታውን በማሸነፍ የውድድሩ አሸናፊ መሆን ችለዋል። 

አምበላቸው ቲሞቲ አዋኒይ እና ወሳኝ አጥቂያቸው ፓትሪክ ካዱን ጨምሮ በርካታ ተጫዋቾች ሳይዙ ወደ ውድድሩ ያመሩት ኬሲሲኤዎች ከዚ በፊት በ1978 ውድድሩን ማሸነፍ ችለው የነበረ ሲሆን የዘንድሮው ሁለተኛ ዋንጫቸው ነው።

ትልቅ ለውጥ እያመጡ የሚገኙት የዩጋንዳ ቡድኖች የዞኑ ዋንጫ ካሸነፉ በርካታ ዓመታት ቢቆጠሩም ኬሲሲኤዎች ለአስራ አራት ዓመታት የቆየው መጥፎ ታሪክ መሰረዝ ችለዋል። ዩጋንዳዎች ለመጨረሻ ግዜ ያነሱት የሴካፋ ክለቦች ዋንጫ በ1995 ሲሆን አሸናፊው ቡድንም ዩጋንዳ ፖሊስ ነበር።