የኢትዮጵያ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ሁለተኛ ቀን ውሎ

ትላንት የተጀመረው የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ዛሬም ሲቀጥል በሁለት ሜዳዎች ስምንት ጨዋታዎች ተከናውነዋል።

03:00 በወጣት ማዕከል ካማሽ ከተማ ከምዕራብ ዐባያ ያደረጉት ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ተደርጎበት 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። በክልላቸው በተፈጥሮ ያገኙት አቅም እንዳለ ያሳዩን ሁለቱ ቡድኖች እጅግ ጠንካራ ፉክክር አሳይተውናል። በመጀመርያው አጋማሽ በሁሉም ረገድ የተሻሉ የነበሩት ምዕራብ ዐባያዎች ዳዊት አየለ ባስቆጠራት ጎል መምራት ሲችሉ ተጨማሪ ጎል ፍለጋ ተጭነው ቢጫወቱም ሳይሳካላቸው ቀረ እንጂ እንቅስቃሴያቸው መልካም ነበር። ካማሾች በተደጋጋሚ ወደፊት በመሄድ የጎል እድል መፍጠር ላይ ቢቸገሩም አልፎ አልፎ በአጥቂዎቻቸው አማካኝነት ጫና ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል።

ከእረፍት መልስ የጨዋታው እንቅስቃሴ ተቀይሮ ምዕራብ ዐባያዎች ተዳክመው ሲቀርቡ ካማሾች በተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያደርጉት የነበረው ጥረት ተሳክቶላቸው ተቀይሮ በገባው አጥቂያቸው ሰይድ አማካኝነት ከማዕዘን ምት የተላከው ኳስ በተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ አግኝቶ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ችለዋል። የጨዋታውን ሚዛን ተቆጣጥረው ጥሩ መንቀሳቀስ ቢችሉም ካማሾች አሸንፈው ሊወጡ የሚችሉበትን ጎሎች ሳያስቆጥሩ፣ ምራዕብ ዐባያዎችም በተወሰደባቸው ብልጫ የተጫዋቾች ቅያሪ በተደጋጋሚ ቢያደርጉም ብዙም ለውጥ ማሳየት ሳይችሉ ጨዋታው ተጨማሪ ጎል ሳያስመለክተን 1-1 አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

05:00 በቀጠለው የወጣት ማዕከል ሁለተኛ ጨዋታ መከላከያ እና ዶዶላ ከተማ ተገናኝተው በመከላከያ የበላይነት 4-0 ተጠናቋል። ይህ ጨዋታ በተደጋጋሚ በክልል ክለቦች ውድድር ላይ እየተሳተፈ ወደ አንደኛ ሊግ ለማደግ እየተቸገረ የሚገኘው ዶዶላ ከተማ እና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ብቻ ባሳተፈው የተጫዋቾች ስብስብ በመያዝ በትልቅ ውድድር ላይ የመጀመርያውን ተሳትፎ ያደረገው መከላከያን ያገናኘ ነበር።

ጨዋታው በሁለቱም በኩል ቀዝቀዝ ብሎ ቢጀምርም በአንፃራዊነት ዶዶላዎች በተሻለ በመንቀሳቀስ የጎል ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። ሆኖም የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሲሄድ እና ቡድኑ በጨዋታው እየተቀናጀ ሲመጣ የዶዶላን በር መፈተሽ የጀመሩት መከላከያዎች ነፃ ጎል መሆን የሚችሉ ሁለት ዕድሎችን ከግብጠባቂው ጋር ተገናኝተው ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። በዚህ ጥቃታቸው የቀጠሉት መከላከያዎች ያገኙትን የማዕዘን ምት በተከላካዮች ተደርቦ ሲመለስ ከሳጥን ውጭ በግራ እግሩ በጥሩ ሁኔታ መሣርያ ዱሬሳ በቀጥታ ወደ ጎል መቶ ባስቆጠራት ጎል መምራት ጀምረዋል። ብዙም ሳይቆይ አጥቅተው መጫወታቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች በቀጣይ ዓመት ዋና ቡድኑን ይቀላቀላሉ ተብሎ እየተነገረላቸው ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል ባለ ግራ እግሩ ተስጦ ተጫዋች የሆነው አማካይ ዳንኤል ኃ/ማርያም ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ አምስት ከሃምሳ ውስጥ በመቀስ ምት ግሩም ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው ወደ እረፍት አምርቷል።

በሁለተኛው አጋማሽ ዶዶላዎች እስከ 60ኛው ደቂቃ ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ለማጥቃት ቢሞክሩም የመከላከያው ታረቀኝ ጉሌ ከተከላካዮች መሐል ሾልኮ በመግባት ሦስተኛ ጎል አስቆጥሮ የዶዶላን እንቅስቃሴ አውርዶታል። ጨዋታው ቀዝቀዝ ብሎ ቀጥሎ ወደ መጨረሻው ደቂቃ ላይ ዮናስ ኃ/ማርያም አራተኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በመከላከያ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሌሎች የክልል ክለቦች ሻምፒዮና የዛሬ ውጤቶች

አሳይታ ከተማ 1-2 አባድር ሠላም
ኤጀሬ ከተማ 2-3 አቃቂ ማዞርያ
አኳ ድሬ 0-2 ሾኔ ከተማ
02 ቀበሌ ድሬደዋ 0-2 ኣብዲ ሱሉልታ
ደጋ ዳሞት 2-2 ኮረም ከተማ
ጂኮ ከተማ 9–1 ሐረር ሶፊ

ማክሰኞ ሐምሌ 16 ቀን 2011

03:00 | ሰመራ ሎግያ ከ ሐውዜን ከተማ (ወጣት ማዕከል)

03:00
| አሳሳ ከተማ ከ አዲስ ከቴ (አበበ ቢቂላ)

05:00 | ሐረር ቡና ከ ሞጣ ከተማ (ወጣት ማዕከል)

05:00
| ድሬደዋ 04 ከ ሸዋሮቢት ከተማ (አበበ ቢቂላ)

07:00 | ባምባሲ ከተማ ከ ሲልቫ (ወጣት ማዕከል)

07:00
| መንጌ ቤላሻንጉል ከ ዓድዋ ውሃ አገልግሎት (አበበ ቢቂላ)

09:00 | ፍራውን ከተማ ከ ዳውሮ አላላ (ወጣት ማዕከል)

09:00
| አሚር ኑር ከ ሙኩውይ (አበበ ቢቂላ)


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡