ለ4ኛ ጊዜ በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሀገር ውስጥ ተጨዋቾች ብቻ ለሚካፈሉበት የአፍሪካ ሃገራት ዋንጫ (ቻን) ትላንት 10፡00 ላይ በኪጋሊ ተጀምሯል፡፡
በምድብ ሁለት ከዲ. ሪ. ኮንጎ ፣ አንጎላ እና ካሜሩን ጋር የተደለደለው ብሄራዊ ቡድናችን ዛሬ በ10፡00 የምድቡን የመክፈቻ ጨዋታ ከዲ. ሪ. ኮንጎ ጋር ያደርጋል፡፡ ዲ.አር.ኮንጎ በአፍሪካ መድረክ በጠንካራ ተፎካካሪነታቸው የሚታወቁ ክለቦችን በመያዝ ይታወቃል፡፡ አሰልጣኙ ኤ.ኤስ. ቪታ ከተባለው ክለብ 8 ተጨዋቾችን ሲመርጡ አንጋፋው ቲፒ ማዜምቤ 3 ተጨዋቾችን ብቻ ነው ማስመረጥ የቻለው፡፡
በተቃራኒው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከመረጣቸው 23 ተጨዋቾች ከአብዛኛዎቹ የሊጉ ክለቦች ለማካተት ተሞክሮዋል፡፡ ሊጉ ላይ ካሉት 14 ክለቦች መካከል 3 ክለቦች ብቻ ናቸው ለብሄራዊ ቡድኑ ተጨዋች ማስመረጥ ያልቻሉት (ኤሌክትሪክ ፣ ድሬደዋ ከነማ ፣ ሀዲያ ሆሳህና)፡፡
አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ወደ ሩዋንዳ ይዘውት ያመሩት የተጨዋቾች ስብስብ ብዙዎቹ የስፖርት ቤተሰቦችን ያስደሰተ እና ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚቻል መልኩ ወቅታዊ ብቃትን ያማከለ እንደሆነ ቢነገርለትም አንዳንድ ተቺዎች ደግሞ በርካታ ሃገራት ቻንን ከሚጠቀሙበት አላማ አንፃር ለምን እንደ ሴካፋው ሁሉ ወጣት እና ልምድ የሌላቸው ተጨዋቾችን አብዝተው እንዳልተጠቀሙ ይናገራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በዚህ ውድድር ላይ ለተከታታይ ሁለታኛ ጊዜ ነው የሚሳተፈው፡፡ ቡድኑ በ2014 በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እየተመራ ተሳታፊ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዛ ውድድር ላይ ቡድኑ የምድቡን ሶስት ጨዋታዎች አድርጎ በሶስቱም ጨዋታ ተሸንፎ ምንም ግብ በተጋጣሚው መረብ ላይ ሳያስቆጥር ያለምንም ነጥብ እና በ4 የግብ እዳ ከምድቡ የመጨረሻ ደረጃን በመያዝ ከምድቡ መሰናበቱ ይታወሳል፡፡
አሰልጣኝ ዮሀንስ ሳህሌ ወደ ሩዋንዳ ከማምራታቸው በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እቅዳችሁ ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ሲቀርብላቸው ከባለፈው ማለትም ከ2014ቱ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ነው የምናስበው ሲሉ ነበር ምላሽ የሰጡት፡፡
ቡድኑ አሁን ሩዋንዳ በሙሉ ጤነኝነት እንደሚገኝ ከሩዋንዳ የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ አዲስ አበባ እያሉ ጉዳት የነበረባቸው እንደ ታፈሰ ተስፋዬ አይነት ተጨዋቾችም በሙሉ ጤነኝነት ላይ እንደሚገኙ እንደውም ቡድኑ ሩዋንዳ ሲገባ ያደረገውን የመጀመሪያ ልምምድ አብረው እንደሰሩ ተነግሯል፡፡
ጥቂት ስለ ቻን
ቻን እንደሌሎቹ የአፍሪካ አህጉራዊ ውድድሮች እድሜ ጠገብ አደለም፡፡ ውድድሩ በ2009 ነበረ ለመጀመሪያ ጊዜ በአይቮሪ ኮስት አስተናጋጅነት የጀመረው፡፡ እስካሁን 3 ጊዜያት በተከናወነው ይህ ውድድር አሸናፊ የነበሩት በ2009 ዲ.አር.ኮንጎ በ2011 ቱኒዚያ እና በ2014 ሊቢያ ናቸው፡፡
2009 ላይ ውድድሩ ሲጀመር በየሁለት አመቱ በጎዶሎ ቁጥር እንዲከናወን ነበር የተፈለገው፡፡ ነገር ግን ከ2012 በኃላ የአፍሪካ ዋንጫ በየጎዶሎ ቁጥር አመታት እንዲደረግ ስለተወሰነ ቻን ጊዜውን ቀይሮ ደቡብ አፍሪካ ካዘጋጀችው የ2014 ውድድር ጀምሮ በየሙሉ ቁጥር አመታት እንዲዘጋጅ ተወስኗል፡፡
ውድድሩ ላይ ከሚሳተፉት ሀገራት ከምድብ 2 ዲ.ሪ.ኮንጎ እንዲሁም ከምድብ 4 ዚምባቡዌ እስካሁን ድረስ በሁሉም የቻን ውድድር ላይ የተሳተፉ ሀገራት ናቸው፡፡ ዲ.ሪ.ኮንጎ ምን ያህል ጠንካራ ቡድን እንደሆነ ለመናገር በቂ ይመስለናል፡፡ ከዛ በተጨዋሪ የውድድሩን ዋንጫ አንድ ጊዜ ማንሳትም ችለዋል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ አስተናጋጅ የሆነችው ሩዋንዳ ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ለማዘጋጀት 22 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ወጪ አድርጋለች፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የምድቡን የመጀመርያ ጨዋታውን ዛሬ 10፡00 ሰአት ላይ በስታዴ ሁዬ ስታዲየም ያደርጋል፡፡ ስታዴ ሁዬ የሰው ሰራሽ ሳር የተተከለበት በቡታሬ ከተማ የሚገኝ ስታዲየም ነው፡፡