አለልኝ አዘነ ከመቐለ ጋር ሲለለያይ አልሀሰን ካሉሻ ቡድኑን ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ተቀላቅሏል

መቐለ ከአዲስ ፈራሚው ጋር ሲለያይ ሦስት ተጫዋቾች ቅድመ ዝግጅቱን ተቀላቅለዋል።

ባለፈው ሳምንት መቐለ 70 እንደርታ ለመቀላቀል ተስማምቶ ከቡድኑ ጋር ልምምድ ሲሰራ የቆየው አለልኝ አዘነ በጥቅማ ጥቅሞች ዙርያ ባለመስማማቱ ከቡድኑ ጋር ተለያይቷል። ባለፉት ዓመታት በአርባምንጭ ከተማ ቆይታ ያደረገው እና ለአዲሱ ቡድኑ ጨዋታ ሳያደርግ የተለያየው መለሎው አማካይ ቀጣይ ማረፍያው በቅርቡ ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል።

በሌላ ዜና ቀድሞ ወደ ቡድኑ ለመቀላቀል የተስማማው ካሉሻ አልሃሰን ወደ መቐለ አምርቶ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን ሲቀላቀል ሥዩም ተስፋዬ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ እና እንዳለ ከበደ ሌሎች ከዕረፍት ዘግይተው ቡድናቸው የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ሆነዋል።

በተያያዘ ዜና ማሊያዊው አጥቂ ሙሳ ካማራ ቡድኑን በቅርብ ቀናት ይቀላቀላል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ ቀደም ለኢስማዒልያ እና ለራዮን ስፖርትስ መጫወት የቻለው ይህ ተጫዋች በአንድ ወቅት ከባዕድ አምልኮ ጋር በተያያዘ ምክንያት የዓለም መነጋገርያ ሆኖ ነበር። ተጫዋቹ የጎል ድርቅ አጋጥሞት በነበረበት ወቅት በተቃራኒ የግብ ክልል ውስጥ ከቀበረው ባዕድ ነገር ጋር በተያያዘ ነበር መነጋገርያ ሆኖ የነበረው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡