ከማል አካዳሚ ሁለተኛውን ማሰልጠኛ በወራቤ ከፍቷል

በቀድሞው አንጋፋ አሰልጣኝ ከማል አህመድ ስም በሀዋሳ ተከፍቶ ሲሰራ የቆየው የከማል የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ አካዳሚ በወራቤ ከተማ ሁለተኛውን ማሰልጠኛ ከፍቷል፡፡

የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ ከአራት ዓመት በፊት በሀዋሳ ከተማ ከ13-15 ዓመት ያሉ በሁለቱም ጾታ 200 ታዳጊዎችን በማቀፍ የጀመሩ ሲሆን በዚህም አበረታች ስራዎችን እየሰሩ ለሀዋሳ ከተማ ክለብ የታዳጊ ቡድን ተጫዋቾችን በማፍረት ላይ ይገኛሉ፡፡ አሰልጣኙ አሁን ደግሞ በትውልድ ከተማቸው ወራቤ ላይ ከማል እግር ኳስ አካዳሚ (ቁጥር 2) በማለት ከቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ግብ ጠባቂ እና በሀዋሳ አሰልጣኝነታቸው አብሮ ከነበረው ሳዳት ጀማል ጋር በመሆን ከትላንት በስቲያ በከተማዋ በይፋ ተከፍቷል፡፡

በዕለቱ በክብር እንግድነት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጂራ እና የስልጤ ዞን ባህል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ኃላፊ አቶ መሐመድ በርጋጋ ተገኝተው አካዳሚውን በይፋ አስጀምረውታል፡፡ በእለቱም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የደቡብ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ለአካዳሚው በርካታ የትጥቅ፣ ኳስ እና ተያያዥ ቁሳቁሶች በድጋፍ መልክ አበርክቷል፡፡

አሰልጣኝ ከማል ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፁት “የተደረገልን ድጋፍ ቀላል አይደለም። ዞኑ የሰጠን ትኩረት ከፍተኛ ነው። እኔም የተሰጠኝን እድሜ ሳያግደኝ ለመስራት ከአሁኑ ዝግጁ ሆኛለሁ።” ብለዋል። አብሯቸው ይህን አካዳሚ በትብብር የሚሰራው ሳዳት ጀማል በበኩሉ “እኛ ያለፍንበትን ማንም ማለፍ የለበትም። በዘመናዊ ደረጃ በሚሰጡ ስልጠናዎች ታግዞ ለመስራት ከታሰበ እንደዚህ ዓይነት አካዳሚዎች መከፈታቸው በቀላሉ ሊታዩ አይገባም። እኛም ለመስራት ዝግጁ ነን ብሏል። ” የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ በበኩላቸው ፌዴሬሽኑ በቀጣይ ጊዜያት በታዳጊ ላይ ለመስራት ቆርጦ እንደተነሳ ገልፀው አመራሮች ትኩረት እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል። የስልጤ ዞን የስፖርት ኃላፊው አቶ መሐመድ ደግሞ ይህ አካዳሚ መከፈቱ በሁሉም ወረዳዎች ላይ ተደብቀው ያሉ ተስፈኛ ወጣቶችን የሚያወጣ በመሆኑ ዞኑ በሁሉም ረገድ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ማዕከሉ ዕድሜያቸው ከ8-17 ዓመት ለሆኑ ታዳጊዎች በሳምንት ለስድስት ቀናት ስልጠና የሚሰጥ ሲሆን 250 የሚደርሱ ታዳጊዎችን በሁለቱም ፆታ አቅፎ ይሰራል ተብሏል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡