አዳማ አንድ ተጫዋች ሲያስፈርም የነባሮችን ውል አደሰ

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ከቀጠረ በኋላ ወደ ዝውውር ገበያው የገባው አዳማ አራተኛ ተጫዋቹን ሲያስፈርም የአራት ነባር ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል፡፡

በ2009 የውድድር ዘመን ጅማሮ ኢትዮጵያ መድንን በመልቀቅ ወደ ድሬዳዋ ያመራው አጥቂው ሐብታሙ ወልዴ በቆይታው ወሳኝ ጎሎችን ለቡድኑ ያስቆጠረ ሲሆን ከአማኑኤል ጎበና፣ አስናቀ ሞገስ እና ታሪክ ጌትነት በመቀጠል አራተኛው የአዳማ አዲስ ተጫዋች ሆኗል። ዳዋ ሆቴሳን በጉዳት ባጣባቸው ወቅቶች ሲቸገር የታየው የቡድኑ የአጥቂ መስመርን እንደሚያጠናክርም ይጠበቃል።

አዳማ ከተማ ከአዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ ነባሮቹን ውል ማደስ ጀምሯል፡፡ በዚህም መሠረት አምበሉ እና የግራ መርመር ተከላካዩ ሱሌይማን መሐመድ፣ የመሐል ተከላካዩ ተስፋዬ በቀለ እንዲሁም አማካዮቹ አዲስ ህንፃ እና ኤፍሬም ዘካሪያስ በአንድ ዓመት ተጨማሪ ውል በአዳማ ቆይታ ያደርጋሉ፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡