ወልዋሎ ተጨማሪ ሦስት ተጫዋቾችን አስፈረመ

የአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌን ውል በማራዘም የዝውውር እንቅስቃሴ የጀመሩት ቢጫ ለባሾች ሦስት ተጨማሪ ተጫዋቾች በማስፈረም የአዳዲስ ተጫዋቾችን ቁጥር ስድስት አድርሰዋል።

ተስፈኛው ተከላካይ ዳዊት ወርቁ ከፈራሚዎቹ አንዱ ነው። ባለፈው ዓመት ሳይጠበቅ የደደቢት የተከላካይ ክፍል በብቃት መምራት የቻለው ይህ ወጣት የመሐል ተከላካይ በኦሊምፒክ ብሔራዊ ተመርጦ መጫወት ችሏል። ከደደቢት ወጣት ቡድን ወጥቶ ባለፈው ዓመት ከተለያዩ ተጫዋቾች ጋር ተጣምሮ መጫወት የቻለው ይህ ተጫዋች በአሰልጣኙ ወሳኝ ቦታ ላይ ለመሰለፍ ከበርካታ ተጫዋቾች ብርቱ ፉክክር ይጠብቀዋል። ዳዊት ከመሐል ተከላካይነት በተጨማሪ በመስመር ተከላካይነትም መሰለፍ ይችላል።

ሌሎች ቡድኑን የተቀላቀሉት ተጫዋቾች የተጠናቀቀው የውድድር ዓመትን በከፍተኛ ሊጉ ክለብ ኢትዮጵያ መድን ያሳለፉት ሚካኤል ለማ (ፎቶ-ግራ) እና ዘሪሁን ብርሀኑ (ፎቶ-ቀኝ) ናቸው። ከዚህ ቀደም ለደቡብ ፖሊስ እና ድሬድዋ ከተማ የተጫወተው ሚካኤል የፈጠራ ችግር የሚስተዋልበትን የመሐል ክፍል እንደሚያሻሽል ይጠበቃል። የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ፣ ሰበታ ከተማ እንዲሁም የወጣት ብሔራዊ ቡድን አማካይ ዘሪሁን ብርሀኑም ወደ አዳማ የተጓዘው አማኑኤል ጎበናን ቦታ እንደሚሸፍን ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡