ይሁን እንደሻው አዲስ አዳጊዎቹን ተቀላቅሏል

በቀጣዩ የውድድር ዓመት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ መሆናቸውን ያረጋገጡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ለቀጣዩ የውድድር ዘመን ቡድናቸው በማጠናከር ላይ ይገኛሉ ፤ በዛሬው ዕለትም የቀድሞው የጅማ አባጅፋር የአማካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነውን ይሁን እንደሻውን ማስፈረም ችለዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በመተሐራ ስኳር እና ድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም ያለፉትን ሁለት ዓመታት ደግሞ በጅማ አባ ጅፋር የተሳካ ጊዜያትን ያሳለፈው ይሁን እንደሻው በተለይም በ2010 ቡድኑ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ ከፍተኛውን ሚና የተወጣ ሲሆን በተጨማሪም በ2008 ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በግሉ ድንቅ የውድድር ጊዜን ማሳለፍ ችሏል። በዚህም በወቅቱ በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ይመራ በነበረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተደጋጋሚ ጥሪ ቀርቦለት ሀገሩን መወከል ችሏል፡፡

የአሰልጣኝ ግርማ ታደሰን ውል በማደስ የዝውውር እንቅስቃሴያቸውን የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከዚህ ቀደም ደስታ ጊቻሞ፣ ብሩክ ኤልያስ፣ አብዱልሰመድ ዓሊ እና ሄኖክ አርፊጮን ማስፈረማቸው ይታወሳል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡