የትግራይ እና የባህር ዳር ስታዲየሞች አህጉራዊ ጨዋታዎችን ለማከናወን ፍቃድ አገኙ

የትግራይ ስታዲየም ለመጀመርያ ጊዜ የካፍ ጨዋታዎች ለማከናወን እውቅና ሲያገኝ የባህርዳር ስቴዲየምም በድጋሚ ፍቃዱን አግኝቷል።

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የሚገኙ ስታዲየሞች ዝቅተኛው የካፍ መመዘኛ ማሟላት አይችሉም በማለት ሁሉንም ሜዳዎች ከአህጉራዊ ጨዋታዎች ማገዱ ይታወሳል። ዛሬ ደግሞ የትግራይ እና የባህርዳር ስታዲየሞች የካፍ መመዘኛን በከፊል በሟሟላታቸው በእግር ኳስ አወዳዳሪው አካል ጨዋታዎችን ለማካሄድ ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል።

ስታዲየሞቹ ፍቃድ ቢያገኙም በርካታ ያላሟሉት መመዘኛ እና በፍቃድ ሰጪው አካል እንዲሻሻሉ የተነገሩ በርካታ ነገሮች እንዳሉ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የክለብ ላይሰንሲንግ ዲፓርትመንት ዳይሬክተር ተድላ ዳኛቸው (ዶ/ር) አሳስበዋል። “አሁንም ጨዋታ እንዲደርግ የተፈቀደው በጊዜ ገደብ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። እስከ ኦክቶበር (ጥቅምት) ድረስ በሁለቱ ሜዳዎች ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች እንዲደረጉ ካፍ ፍቃድ ሰጥቷል። ከዛ በኋላ ግን የስታዲየሞቹ ደረጃ በድጋሚ ተገምግመው መመዘኛዎቹን ካላሟሉ ፍቃድ አይኖራቸውም። የሚመለከታቸው አካላት ይህን ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል። ” ብለዋል።

ባለፉት ሳምንታት መመዘኛውን ለማሟላት በማሻሻል ሥራ ላይ የነበረው ትግራይ ስታድየም ከሁለት ሳምንት በኋላ መቐለ ከካኖ ስፖርት በሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ የመጀመርያውን አህጉራዊ ግጥሚያ ያስተናግዳል ተብሎ ሲጠበቅ በተደጋጋሚ ሀገራዊ እና የክለብ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎች የተካሄዱበት የባህርዳር ስታዲየም ደግሞ ፋሲል ከነማ ከአዛም በመጪው እሁድ፤ እንዲሁም በኦሊምፒክ ሴቶች እግርኳስ ማጣርያ ኢትዮጵያ ከካሜሩን የሚያደርጉትን ጨዋታ የሚያስተናግድ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡