የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የማጠቃለያ ውድድር ሁለተኛ ቀን ውሎ


በአዳማ እየተካሄደ በሚገኘው ከ20 ዓመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ዛሬ በሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ሲቀጥል አፍሮ ፅዮን፣ ሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ድል ቀንቷቸዋል።

04:00 በጀመረው የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ አዳማ ከተማን ከ ወላይታ ድቻ አገናኝቶ በመጫወት ፍላጎት የተሻሉ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል። የተደራጀ ቡድን ከተስፈኛ ተጫዋቾች ጋር ይዘው የቀረቡት ድቻዎች አብዝተው ኳሱን ተቆጣጥረው አይጫወቱ እንጂ በሚያገኟቸው አጋጣሚዎች በፍጥነት በመሄድ በሚፈጥሩት አደጋ ከአዳማዎች የተሻሉ ሆነው ውለዋል። ድቻዎች በሁለት አጋጣሚዎች በፍጥነት ወደ ጎል በመሄድ የፈጠሯቸውን አጋጣሚዎች የአዳማው ግብጠባቂው ባያድናቸው ኖሮ ጎል መሆን የሚችሉ ነበሩ። በእጅጉኑ የመጫወት ፍላጎታቸው የወረደ ከመሆኑ ባሻገር በራሳቸው ሜዳ እና በመሐል ሜዳ ብቻ ኳሱን ከመነካካት ወደ ፊት በመሄድ የተቸገሩት አዳማዎች በመጀመርያው አርባአምስት ምንም የፈጠሩት የግብ አጋጣሚ አልነበረም። ወደ እረፍት መዳረሻ 43ኛው ደቂቃ የተገኘውን ቅጣት ምትም ዘሪሁን ግሩምነህ በግንባሩ በመምታት ለወላይታ ድቻ የመጀመርያ ጎል አስቆጥሯል ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።


በሁለተኛው አጋማሽ ገና በ49ኛው በአንድ ሁለት ቅብብሎሽ አስራ ስድስት ከሃምሳ ውስጥ በመግባት የግብጠባቂውን አቋቋም ተመልክቶ ንጉሴ ተከስተ ሁለተኛ ጎል ለወላይታ ድቻ ማስቆጠር ችሏል። ከዚህ ጎል መቆጠር በኋላ የጨዋታው እንቅስቃሴ ተቀዛቅዞ የቀጠለ በመሆኑ ብዙም ሳቢ ነገሮችን መመልከት አልቻልንም። ይህም ቢሆን በቀሩት ደቂቃዎች በታምራት ስላስ የሚመራው የወላይታ ድቻ የማጥቃት እንቅስቃሴ በአንድ አጋጣሚ ታምራት ከተከላካዮች መሐል ቆርጦ በመግባት የአዳማ ግብጠባቂ የዳነበት ተጠቃሽ ሙከራ ነበር። ለሁለት ተከፍሎ በተካሄደው ከ20 ዓመት በታች ውድድር በምድብ ሀ እስከ መጨረሻው ጨዋታ ድረስ የዋንጫ ተፎካካሪ ሆኖ የቆዩት አዳማ ከተማዎች በዛሬ ጨዋታ ላይ ያሳዩት እንቅስቃሴ ደካማ አጨዋወት በወላይታ ድቻ 2-0 እንዲሸነፉ አድርጓቸዋል። ውጤቱን ተከትሎ ወላይታ ድቻ በዙር በሚጠናቀቀው በዚህ ውድድር ተከታታይ ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ ምድቡን በቀዳሚነት እንዲመራ አስችሎታል።

06:00 ከበድ ባለ የሙቀት አየር የተካሄደው የመከላከያ እና ሀዋሳ ከነማ ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር አስመልክቶን በሀዋሳ ከነማ 2-1 በሆነ አሸናፊነት ተጠናቋል። ጥሩ ፉክክር በተመለከትንበት በዚህ ጨዋታ ሀዋሳዎች በረዣዥም እና በቆሙ ኳሶች የጎል ዕድሎችን ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ በአንፃሩ መከላከያዎች ኳሱን ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። ከቆመ ኳስ ፀጋአብ ዮሐንስ በግንባሩ ገጭቶ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት የጨዋታው የመጀመርያ ሙከራ የነበረ ሲሆን በ22ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር ወደ ፊት በመግባት የተሻገረውን ኳስ አጥቂው መሐመድ አበራ ጎል በማስቆጠር መከላከያን መሪ ማድረግ ችሏል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ተስፈኛ ተጫዋች መሆኑን በማሳየት ላይ የሚገኘው እና በዋናው የብሔራዊ ቡድን በመጀመርያው ጥሪ ጅቡቲ ላይ ባሳለፍነው ሳምንት የመጀመርያውን ጎል ማስቆጠር የቻለው የሀዋሳው መስፍን ታፈሰ ከተከላካዮች የተጣለለትን በፍጥነት በመግባት የበረኛውን አቋቋም አይቶ ወደ ጎል የላካት ኳስ አቅጣጫዋን ስታ ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣበት ቡድኑን አቻ ማድረግ የምትችል አጋጣሚ ነበረች። በተመሳሳይ ብዙም ሳይቆይ መስፍን ፍጥነቱን ተጠቅሞ ከግብጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ የምታስቆጭ ሆና አልፋለች።

ከእረፍት መልስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተጭነው የተጫወቱት ሀዋሳዎች ጥረታቸው ተሳክቶ ከተሻጋሪ ኳስ ሐብታሙ መኮንን ባስቆጠረው አቻ መሆን ችለዋል። ከመጀመርያው አጋማሽ ቀዝቀዝ ያሉት መከላከያዎች መረጋጋት ተስኗቸው ብዙም ሳይቆዩ ሁለተኛ ጎል ለማስተናገድ ተገደዋል። 65ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ መንገድ በቁጥር በዝተው የመከላከያ የግብ ክልል የደረሱት ሀዋሳዎች የመጀመርያውን ጎል ባስቆጠሩበት ተመሳሳይ መንገድ ከቀኝ መስመር በተሻገረ ኳስ የመጀመርያውን ጎል ያስቆጠረው ሀብታሙ መኮንን ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል። መከላከያዎች የአቻነት ጎል ፍከጋ ጥት ቢያደርጉም ሳይሳካለቸው ቀርቶ በአንፃሩ ሀዋሳዎች ተጨማሪ ጎሎችን ማስቆጠር የሚችሉበትን እድሎች ሳይጠቀሙ ቀርተው በመጨረሻም ከመመራት ተነስተው ጨዋታው በሀዋሳዎች 2–1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

08:00 በቀጠለው የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ፋሲል ከነማን ከአፍሮ ፅዮን አገናኝቶ በቀዘቀዘ እንቅስቃሴ አፍሮ ፅዮን 2-0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። ባልተደራጀ እንቅስቃሴ በተካሄደው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በ6ኛው ደቂቃ ከአፍሮ ፅዮን በኩል ሮብሰን ደምሰው ከርቀት የግብጠባቂውን አቋቋም አይቶ የመታው ኳስ ለጥቂት በግቡ ቋሚ ጠርዝ የወጣበት የጨዋታው የመጀመርያው የግብ ዕድል ነበር። በዐፄዎቹ በኩል አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ብዙም ወደፊት ለመሄድ ቢቸገሩም ናትናኤል ማስሻ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ፋሲል ማሩ በግንባሩ በመግጨት ወደ ጎል የመታው ለጥቂት ወደ ውጭ ወጥቶበታል።

ከእረፍት መልስ በአፍሮ ፅዮን በኩል በግሉ ጥሩ መንቀሳቀስ የቻለው አምበሉ እንድርያስ ለገሰ ከርቀት ከ48ኛው ደቂቃ ግሩም ጎል አስቆጥሮ አፍሮ ፅዮንን ቀዳሚ አድርጓል። ብዙም ሳይቆይ በአንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ የገባው እንድርያስ ለገሰ በግብጠባቂው አናት ላይ ኳሱን በማሳለፍ ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል በ59ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል። ፋሲል ከነማዎች በኩል የመስመር አጥቂ የሆነው ሐብታሙ አስማረ በግሉ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጭ እንደ ቡድን ብዙ መስራት የሚጠበቅባቸው መሆኑ በጉል የታየ ሲሆን በተቃራኒው የግብጠባቂው ዳንኤል ስጦታው ብቃት ባይጨመርበት ኖሮ አፍሮ ፅዮኖች ተጨማሪ ሌሎች ጎሎችን ባስቆጠሩ ነበር። በመጨረሻም ብዙም የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው በአፍሮ ፅዮን 2-0 በሆነ ውጤት አሸናፊነት ተጠናቋል።

በዛሬው ዕለት በተካሄዱት ሦስት ጨዋታዎች የየቡድኖቹ ዋና አሰልጣኞች እና የብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጨዋታዎቹን መከታተላቸው ለወደፊቱ ለተጫዋቾቹ መልካም አጋጣሚ ሆኖ ሲታይ ከዚህ በተጨማሪ መስከረም መጀመርያ ላይ በዩጋንዳ አስተናጋጅ እንደሚካሄድ በሚጠበቀው የሴካፋ ካፋ ከ20 ዓመት በታች ውድድር አሰልጣኝ ዮሴፍ ተጫዋቾችን ለመልመል በስፍራው ተገኝተው ተመልክተናል።

ቀጣይ ጨዋታዎች

ሐሙስ ነሐሴ 9 ቀን 2011
04:00
| ሀዋሳ ከተማ ከ አፍሮ ፅዮን

06:00
| ወላይታ ድቻ ከ ፋሲል ከነማ

08:00
| አዳማ ከተማ ከ መከላከያ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡