የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ አራተኛ የጨዋታ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ቀን ጨዋታዎች ቅዳሜ ተካሂደው ተከታታይ ድሉን ያስቀጠለው ወላይታ ድቻ ዋንጫውን ለማንሳት ሲቃረብ፣ መከላከያ ደረጃውን አሻሽሏል።

04:00 ላይ የመጨረሻዎቹን ሁለት ደረጃዎች ይዘው የተገናኙት አዳማ ከተማ እና ፋሲል ከነማ 1-1 ተለያይተዋል። የተቀዛቀዘ ፉክክር የታየበት ይህ ጨዋታ በተለይ በመጀመርያው አጋማሽ የነበረው እንቅስቃሴ በመሐል ሜዳ የተገደበ ነበር። በዚህም ሁለቱም ቡድኖች ከርቀት በሚያደርጓቸው ሙከራዎች የጎል ዕድል ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በ14ኛው ደቂቃ እዮብ ማቴዎስ ከቀኝ መስመር አክርሮ መትቶ ወደ ውጪ የወጣበት እና አቤኔዘር ሲሳይ ከተመሳሳይ ቦታ ሞክሮ ቋሚ ለትሞ የወጣበት ኳሶችም አዳማዎች ያደረጓቸው ሙከራዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ፋሲል ከነማዎች በጥሩ ሁኔታ ጅማሮን አድርገዋል። በተለይም የመጀመርያዎቹን 15 ደቂቃዎች ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን 61ኛው ደቂቃ ላይም ከመስመር የተሸጋገረውን ኳስ ናትናኤል ማስረሻ አስቆጥሮ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ከጎሉ በኋላ ጨዋታው ተመልሶ የመቀዛቀዝ መልክ ያሳየ ሲሆን ወደ ፊት በተደጋጋሚ ሲጓዙ የነበሩት አዳማዎች በ74ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ፍቅር ደመላሽ በጥሩ አጨራረስ ባስቆጠረው ጎል አቻ መሆን ችለዋል። በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ሙከራዎች ሲደረጉ በአዳማ በኩል አቤል ደንቡ ከርቀት ሞክሮ ግይ ጠባቂ የመለሰበት፣ በፋሲል በኩል ደግሞ ሄኖክ ነጋ ከቀኝ መስመር ሞክሮ ቋሚ ገጭቶ ወደ ውጪ የወጣበት ተጠቃሽ አጋጣሚዎች ነበሩ። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

በመቀጠል 6:00 ላይ መከላከያን ከ አፍሮ ፅዮን ያገናኘው ጨዋታ በመከላከያ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በመጀመርያው አጋማሽ የበላይነት የነበራቸው መከላከያዎች ጎል ለማስቆጠር ብዙም ሲቸገሩ ያልታየ ሲሆን በሰባት ደቂቃዎች ልዩነት ያስቆጠሯቸው ሁለት ጎሎች ጨዋታውን አቅልሎላቸዋል። በ28ኛው ደቂቃ አቤል ነጋሽ ግብ ጠባቂውን አልፎ ቀዳሚውን ጎል ሲያስቆጥር በ35 ሰለሞን ሙላው ከቅጣት ምት ያሻማው ኳስ በቀጥታ ግብ ሆኖ በ2-0 መሪነት ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ ጨዋታው የተቀዛቀዘ መልክ የነበረው ሲሆን ከርቀት ከሚደረጉ ሙከራዎች ውጪ የሚጠቀስ የተደራጀ የማጥቃት እንቅስቃሴ መመልከት አልቻልንም። የጨዋቻው ልዩነት ፈጣሪ የነበረው አቤል ነጋሽ በ68ኛው ደቂቃ ያስቆጠረው ጎልም የጨዋታውን መልክ የሚገልፅ ነበር። ከግራ መስመር ወደ ውስጥ በመግባት ከሳጥን ውጪ አክርሮ የመታው ኳስ በግሩም ሁኔታ ከመረብ አርፎ መከላከያ 3-0 እንዲመራ አስችሏል። ጨዋቴው በዚህ ውጤት ሊጠናቀቅ ሲቃረብ አፍሮ ፅዮኖች ከልዩነት ማጥበቢያነት ያልዘለለች ጎል በሄኖክ እንዳወቅ አማካኝነት አስቆጥረው ጨዋታው በመከላከያ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉን ተከትሎ መከላከያ ነጥቡን 9 በማድረስ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ከማለቱ በተጨማሪ ዋንጫውን ለማንሳት ወላይታ ድቻን በመጨረሻው ጨዋታ ከ3-0 በላይ በሆነ ልዩነት የማሸነፍ ግዴታ ላይ የተመሰረተ እድል መያዝ ችሏል።

8:00 ላይ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የነበረው የሀዋሳ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ፍልሚያ ግሩም የሆነ ፉክክር አሳይቶን በድቻ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ሀዋሳዎች በ4ኛው ደቂቃ ዳግም ዮሐንስ ከማዕዘን የተሻገረውን የማዕዘን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ አግዳሚው በገጭበትና በድጋሚ ሞክሮ በተመሳሳይ ብረቱን በተመለሰበት ሙከራ አደጋ መፍጠር ሲጀምሩ ብዙም ሳይቆይ ንጉሴ ተከስተ ከመስመር የመታውና ታምራት ስላስ ሳይደርስበት የቀረው ሙከራ በወላይታ ድቻ በኩል ለጎል እጅግ የቀረበ ሙከራ ነበር።

ከእረፍት መልስም በተመሳሳይ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እና ቀልብ ሳቢ ፉክክር የተደረገበት ቢሆንም በጠራ የጎል ሙከራ ረገድ ከሁለቱም በኩል መመልከት አልቻልንም። ከርቀት የተሞከሩ ኳሶችም ኢላማቸውን የጠበቁ አልነበሩም። ጨዋታው ከነበረው ተመጣጣኝነት አንፃር በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ በግብ ጠባቂው እና ተከላካዮች መካከል የተፈጠረውን ያለመናበብ ተጠቅሞ አማኑኤል ኢልሶ በ88ኛው ደቂቃ ባስቆጠረው ጎል ወላይታ ድቻዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው መውጣት ችለዋል። በዚህም ያደረጓቸውን አራት ጨዋታዎች በሙሉ ያሸነፉት ድቻዎች ከመከላከያ የሚያደርጉትን የመጨረሻ ጨዋታ በአቻ ውጤት ማጠናቀቅ አልያም ከ3-0 በታች በሆነ ውጤት መሸነፍ ዋንጫውን ለማንሳት በቂያቸው ይሆናል።

መጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

ሰኞ ነሐሴ 13 ቀን 2011
04:00 | አዳማ ከተማ ከ አፍሮ ፅዮን
06:00 | ፋሲል ከነማ ከ ሀዋሳ ከተማ
08:00 | መከላከያ ከ ወላይታ ድቻ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡