ቶኪዮ 2020 | ሉሲዎቹ የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሠርተዋል

2020 የቶኪዮ አሊምፒክ የቅድመ ማጣርያ ሁለተኛ ዙር ጨዋታቸውን ከካሜሩን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር ባልተለመደ ቀን ነገ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚጫወቱት ሉሲዎቹ የመጨረሻ ዝግጅታቸውን ዛሬ አከናውነዋል።

በአሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ እየተመሩ ከቀናት በፊት በአዳማ ከተማ እና በባህር ዳር ከተማ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ የቆዩት ሉሲዎቹ ከኬንያ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በማድረግ ለካሜሩን ጨዋታ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛል። ዛሬ ረፋድ ላይም ጨዋታቸውን በሚያደርጉበት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመጨረሻ ልምምዳቸውን ሠርተዋል።

ከቡድኑ ጋር ወደ ባህር ዳር ለዝግጅት አብራ አቅንታ ባለችበት ወቅት ባጋጠበማት ድንገተኛ የትርፍ አንጀት ህመም የቀዶ ጥገና ህክምና ያደረገችው ተከላካይዋ ቅድስት ዘለቀ እና ወደ ማልታ ያቀናችው አጥቂዋ ሎዛ አበራ ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆናቸው ሲረጋገጥ በምትካቸው ታሪኳ ደቢሶ እና ትግስት ዘውዴ በመጨረሻ ሰዓት ቡድኑን ተቀላቅለዋል።

መጠነኛ ጉዳት ያስተናገደችው አጥቂዋ ሴናፍ ዋቁማ ለነገው ጨዋታ የመድረሷን ነገር አጠራጣሪ ቢሆንም የቀሩት የቡድኑ አባላት በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛሉ። ያም ቢሆን የቡድኑ ወሳኝ አጥቂ ሎዛ አበራ በነገው ጨዋታ አለመኗሯ በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ክፍተት እንዳይፈጥር ተሰግቷል። ቀለል ባለው የዛሬው የሜዳ ቆይታቸው በነገውን ጨዋታ የመጀመርያ ተሰላፊዎችን በሚጠቁም እና አጥቅተው ለመጫወት ያሰቡ በሚመስል መንገድ ልምምዳቸውን ሰርተዋል።

የካሜሩን ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጨዋታው በሚደረግበት ሜዳ 10:00 ላይ የመጨረሻ ልምምዳቸውን የሚሰሩ ሲሆን ባልተለመደ ቀን ነገ ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 10:00 ላይ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የሚካሄደውን ጨዋታ አራቱም ዳኞች ከኬንያ የጨዋታው ኮሚሽነር ደግሞ ከሱዳን እንደሚመሩት ታውቋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡