የአሰልጣኞች አስትያየት | መቐለ 70 እንደርታ 1-1 ካኖ ስፖርት አካዳሚ

በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ቅድመ ማጣርያ የመልስ ጨዋታ መቐለ 70 እንደርታ ከካኖ ስፖርት ጋር 1-1 አቻ ተለያይቶ በድምር የ3-2 ሽንፈት ወደ ተከታዩ ዙር ሳያልፍ ቀርቷል። የሁለቱ ቡድኖች አሰልጣኞችም ከጨዋታ በኋላ አስተያየቱን ሰጥቷል።

“ከድላችን ጀርባ ያለው ነገር ቡድናችን ህዝባዊና የአካዳሚ ቡድን መሆኑ ነው” ሌቪኢላ አንገዝሙ (የካኖ አሰልጣኞች ቡድን አባል)

ስለ ጨዋታው
ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር። መቐለ በጣም ትልቅ ቡድን ነው፤ ትላልቅ ተጫዋቾችም አሉት። የኛ ቡድን ግን የአካዳሚ ቡድን ከመሆኑ በተጨማሪ በወጣቶች የተገነባ ነው። ከአስራ ዘጠኝ እስከ ሃያ ነው የቡድናችን ተጫዋቾች ዕድሜ።

ስለ ድሉ

ከድላችን ጀርባ ያለው ነገር ቡድናችን ህዝባዊና የአካዳሚ ቡድን መሆኑ ነው። መቐለ ደግሞ መጫወት ከጀመሩ ብዙ ጊዜ ባስቆጠሩ ተጫዋቾች የተዋቀረ ነው። ቡድናችን ደግሞ ብዙ አይነት አጨዋወቶች መጫወት የሚችል ዘመናዊ ቡድን ነው።

ስለ ስታዲየሙ ድባብ

በግሌ የመቐለ ደጋፊዎች አድናቂ ነኝ። በስፖርቱ ብዙ ጉዞዎች አድርጌያለው። ስፔንም ፈረንሳይም ሄጃለው። ከመቐለ ደጋፊ የተሻለው ግን የእንግሊዝ ደጋፊ ብቻ ነው።

“ግብ ለማስቆጠር እና ለማለፍ ከልክ በላይ ያለፈ መጓጓት ነበር” ገ/መድህን ኃይሌ

ስለ ጨዋታው

በአጠቃላይ ጨዋታው መጥፎ ነበር ባይባልም በውጤት ደረጃ ግን ጥሩ አልነበረም። ያላሰብነው ነው ያጋጠመን ስህተቶች በዝተውብን ነበር። በመጀመርያው ዙርም በተመሳሳይ በኛ ስህተት ነበር ግብ ያስቆጠሩት በዛሬው ጨዋታ ድጋሚ ስህተት ላለመስራት በደምብ ነበር ያዘጋጀነው ቡድናችን ግን በጣም ብዙ ስህተቶች ነው የተፈፀመው። ግብ ለማስቆጠር እና ለማለፍ ከልክ በላይ ያለፈ መጓጓት ነበር ፤ በጣም በርካታ ግቦች ስተን በሚገም ሁኔታ ነው አቻ የተለያየነው።

ፍፁም ቅጣት ምት ለመምታት የታየው ነገር

ዓለም ላይ የሚታይ ነገር ነው የተለመደ ነው። እንደ ትልቅ ነገርም መታየት የለበትም። የኛ ፍፁም ቅጣት መቺ ማውሊ ነው፤ መጀመርያ አማኑኤል ይመታ ነበር። በወሳኝ ሰዓት ላይ ከሳተ በኃላ ማውሊ ፍፁም ቅጣት ምት እንዲመታ ነው ያደርግነው፤ ከዛ በኃላም አግብቷል። ከዛ በኃላ ግን አማኑኤል ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እንዲሆን ስለምንፈልግ ሃላፊነት ወስደን እንዲመታ አድርገን ነበር። ፍፁም ቅጣት ምት ማውሊ እንደሚመታ ግን የታወቀ ነው። ማውሊ ፍፁም ቅጣት ምቱ እንዲመታ በማድረጌ ያለመናበብ ተፈጥሯል ማለት አይደለም። ማድረግ ያለብኝን ነው ያደረግኩት።

ቡድኑ ሁለተኛው አጋማሽ ስለተከተለው አጨዋወት

በሁለተኛው አጋማሽ ኳስ ይዘህ መስርተህ ለመጫወት ብትፈልግም ጊዜው ይሄድብሃል። አጨዋወቱም ጎድቶናል ማለት አይደለም። በርካታ ዕድሎች ናቸው የተፈጠሩት። ኃላፊነት መውሰድ ካለብኝ እኔ ነኝ ኃላፊነቱን የምወስደው። ሽንፈት ሲመጣ ሁሉም ወደ አሰልጣኝ ነው የሚጠቋቆመው። ማሸነፍ ላይ ሲሆን ግን አሰልጣኝን የሚያነሳ የለም። ቡድኑ እንዴት እንደመጣ ይታወቃል። ከተጫዋቾቹ ጋር በጋራ ሆነን እዚ ደረጃ ያደረስነውም እኛ ነን። ይህ የእግርኳስ ባህሪ ነው።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡