ሰበታ ከተማ ያስፈረማቸውን አዳዲስ ተጫዋቾች ቁጥር ከፍ አድርጓል

ከሳምንቱ መጨረሻ ጀምሮ በስፋት ወደ ዝውውር ገበያው የገባው ሰበታ ከተማ ተጨማሪ አራት አዳዲስ ተጫዋቾች ሲያስፈርም የሦስት ነባሮችን ውል ማደስ ችሏል።

መስዑድ መሐመድ የክለቡ አዲስ ፈራሚ ከሆኑት መካከል ነው። አንጋፋው አማካይ የውድድር ዓመቱን በጅማ ያሳለፈ ሲሆን ቀደም ብሎ ደግሞ በኢትዮጵያ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድንቅ ጊዜያትን አሳልፏል። በመጪዎቹ ቀናት የቡድኑ አሰልጣኝ እንደሚሆኑ ከሚጠበቁትና በኢትዮጵያ ቡና በጋራ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን ካነሱት ውበቱ አባተ ጋርም ዳግም ይገናኛል።

ወንድይፍራው ጌታሁን ሌላው የቡድኑ አዲስ ፈራሚ ነው። የቀድሞው የኢትዮጵያ መድን የመሐል ተከላካይ ያለፉትን አራት ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና ያሳለፈ ሲሆን ወደ ሰበታ ማምራቱን ተከትሎ በአዲሱ ክለቡ ለመጀመርያ ተሰላፊነት ከጌቱ ኃይለማርያም፣ ታደለ ባይሳ እና አዲስ ተስፋዬ ፉክክር ይጠብቀዋል።

ሳሙኤል ታዬ ሦስተኛው ፈራሚ ነው። የመስመር አማካዩ በኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ያለፉትን 7 ዓመታት በመከላከያ ያሳለፈ ሲሆን እንደ መስዑድ ሁሉ በቡና እያለ የሊጉን ዋንጫ ማሸነፍ የቻለ አማካይ ነው።

አራተኛው የክለቡ አዲስ ተጫዋች ደሳለኝ ደበሽ ሆኗል። የተከላካይ አማካዩ አዳማ ከተማን ለቆ ስሑል ሽረን የተቀላቀለው በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሲሆን ሰበታን የተቀላቀለ ስምንተኛው ተጫዋች ሆኗል።

ከአዳዲስ ተጫዋቾች ጎን ለጎን የነባሮችን ውል በማደስ ላይ የሚገነው ሰበታ ከተማ የናትናኤል ጋንቹላ፣ ሰለሞን ጌታሁን እና እንዳለ ዘውገን ኮንትራት ማራዘሙን ለማወቅ ተችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡