ሪፖርት | ኢትዮጵያ በሜዳዋ ከካሜሩን አቻ ተለያይታለች

ለ2020 ኦሊምፒክ የሴቶች እግርኳስ ውድድር የሁለተኛ ዙር የማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታቸውን ከካሜሩን ጋር ያደረጉት ሉሲዎቹ 1-1 ተለያይተዋል።

አሰልጣኝ ሠላም ዘርዓይ በቅርብ ጊዜያት ቡድኑ ሲጠቀምበት ከነበረው ስብስብ በርከት ያሉ ለውጦችን በማድረግ ለጨዋታው የቀረበች ሲሆን በመጀመርያው አጋማሽ የተዳከመ፣ በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ በአንፃራዊነት የተነቃቃ እንቅስቃሴ ተመልክተንበታል።

ከቅብብል ባለፈ ወደ ማጥቃት ወረዳ እጅግ በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ የደረሱት ሉሲዎቹ በ4ኛው ደቂቃ ለጎል የቀረበ የግብ እድል ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። በሜዳ ላይ ከነበሩት ተጫዋቾች በተሻለ ሁኔታ ኳስን ወደ ተጋጣሚ አደጋ ክልል ለማሻገር ጥረት ስታደርግ የነበረቸረው አምበሏ ብርቱካን ገብረክርስቶስ በጥሩ ሁኔታ የሰጠቻትን ኳስ መዲና ዐወል ተቆጣጥራ ወደ ግብ የመታችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ በእግሯ ተጠቅማ አውጥታባታለች።

ከላይ ከተጠቀሰው ሙከራ ውጪ ሊጠቀስ የሚችል የጎል አጋጣሚ በሁለቱም በኩል ያልተፈጠረ ሲሆን ከርቀት የሚመቱ እና ተሻጋሪ ኳሶችም ኢላማቸውን የሳቱ ነበሩ።

የተሻለ እንቅስቃሴ እና ጎሎች በታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ በርከት ያሉ የግብ ዕድሎች የተፈጠሩ ሲሆን ካሜሩኖች የኢትዮጵያ ተከላካዮችን ስህተት በመጠቀም በተለይ እስከ 65ኛው ደቂቃ ባለው ጊዜ አደገኛ የጎል ማግባት አጋጣሚዎችን ፈጥረዋል።

በ46ኛው ደቂቃ ከዓለምነሽ የተነጠቀውን ኳስ አባም ሚቼሌ በፍጥነት ወደ ሳጥን ይዛ በመግባት የመታችው ኳስ መረቡን ታኮ ወደ ውጪ ሲወጣ ከአምስት ደቂቃዎች በኋላም በተመሳሳይ ብዙዓየሁ ወደፊት ልታሻግረው የነበረው ኳስ ተቋርጦ ፌውጂዮ ራይሳ ያሻገረችላትን ግሩም ኳስ አባም ሚቼሌ በጥሩ አጨራሰስ እንግዶቹን ቀዳሚ አድርጋለች። ለጎሉ መቆጠር የኢትዮጵያ ተከላካዮች የጨዋታ ውጪ አጠባበቅ እና የአቋቋም ስህተት ከፍቸኛ አስተዋፅኦ አድርጓል።

ከጎሉ መቆጠር በኋላም ቀጣዮቹን 15 ደቂቃዎች ካሜሩኖች የጎል ልዩነታቸውን የሚያሰፉ አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር። በ59ኛው ደቂቃ ራይሳ ያሻገረችውን ኳስ ኢካባ ኤዶአ ሳትደርስበት የቀረችው፣ በ60ኛው ደቂቃ ኢካባ ኤዶአ በግራ በኩል ገብታ ያሻገረችውና አባም ሚቼሌ ሞክራ ወደ ውጪ የወጣባት እንዲሁም በ64ኛው ደቂቃ ማቺያ ከመስመር ያሻገረችው እጅግ ለጎል የቀረበ እድል ማንም ሳይደርስበት ወደ ውጪ የወጣው ሙከራ እንግዶቹ ጨዋታውን የሚጨርሱበት አጋጣሚዎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታው ቅኝት ለመግባት የዘገዩት ሉሲዎቹ ሁለቱ የማጥቃት አማካዮች አረጋሽ ከልሳ እና ሰናይት ቦጋለን ካስገቡ በኋላ በሒደት ጥሩ የተንቀሳቀሱ ሲሆን በተሻለ ሁኔታ ወደተጋጣሚ የጎል ክልል መድረስም ችለዋል። በ65ኛው ደቂቃ ዓለምነሽ ያሻገረችውን ኳስ ተከላካይዋ ጆንሰን ኤስቴሌ በግምባሯ ገጭታ ራሷ ላይ ጎል ለማስቆጠር ለጥቂት ስትተርፍ ከአረጋሽ የተሻማውን የማዕዘን ምት መሠሉ ሞክራ ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶባታል።

ከሙከራዎቹ በኋላ የተነቃቁት ሉሲዎቹ ምንም እንኳን በቀሪ ደቂቃዎች ብዙም የጎል አጋጣሚዎች ባያገኙም ጫና በመፍጠር የተሻለ ተጫውተዋል። በ82ኛው ደቂቃ ላይም ተቀይራ የገባችው ምርቃት ፈለቀ ከእጅ ውርወራ የተቀበለችውን ኳስ ተቆጣጥራ ወደ ሳጥን ስትልከው በጨዋታው ተቸግራ የዋለችው ሴናፍ ዋቁማ አመቻችታላት ሰናይት ቦጋለ በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት ቀይራ ኢትዮጵያን አቻ አድርጋለች።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ኢትዮጵያዎች በጎል ሙከራ ያልታጀበ እና ጥድፊያ የተሞላበት ያልተሳኩ የማጥቃት ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን በዚህም ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በ86ኛው ደቂቃ ሌውና ዬቮኔ በሰራችው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ የወጣችበት ክስተትም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች የታየ የሚጠቀስ ክስተት ነው።

ጨዋታው 1-1 መጠናቀቁን ተከትሎ ለሉሲዎቹ ወደ ሦስተኛው የማጣርያ ዙር ማለፍን ፈታኝ ሲያደርግባቸው ካሜሩን ወሳኝ የአቻ ውጤት ይዛ በመጪው እሁድ በመልስ ጨዋታ ያውንዴ ላይ ትጫወታለች።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡