ኢትዮጵያ ቡና የተከላካይ ክፍል ተጫዋች አስፈረመ

በዚህ ሳምንት ወደ ዝውውር ገበያው የገቡት ኢትዮጵያ ቡናማዎቹ የተከላካይ መስመር ተጫዋች የግላቸው አድርገዋል።

በዚህ ዝውውር መስኮት ከበርካታ ተጫዋቾች ተለያይተው በአሰልጣኙ ምርጭ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተጫዋቾች ያስፈርማሉ ተብለው የሚጠበቁት ኢትዮጵያ ቡናዎች በባለፈው ዓመት ከሲዳማ ቡና ጋር ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው ፈቱዲን ጀማልን አስፈርመዋል።

የቀድሞው የሀላባ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ተከላካይ ያለፉት ሁለት ዓመታትን በሲዳማ ቡና ያሳለፈ ሲሆን በ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን እና ኦሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን ተጫውቷል። ከኳስ ጋር ጥሩ የሆነው ተከላካዩ በአዲሱ ክለቡ ከሌላው ክለቡን ከተቀላቀለው ወንድሜነህ ደረጄ ጋርም ጥሩ ጥምረት እንደሚፈጥር ይጠበቃል።

ከሌሎች ቡድኖች አንፃር ሲታይ በዝውውሩ በንቃት እየተሳተፉ የማይገኙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በቀጣይ ቀናት ሌሎች ዝውውሮችም ለማጠናቀቅ በእንቅስቃሴ ይገኛሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ