በሴካፋ ከ15 ዓመት በታች ውድድር ወደ ፍጻሜ ያለፉ ቡድኖች ተለይተዋል

በኤርትራ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የሴካፋ ከ15 ዓመት ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ኬንያ እና ዩጋንዳ ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ የመጀመርያው የሴካፋ ዋንጫን ለማንሳት ተገናኝተዋል።

በ7:30 የተካሄደው ጨዋታ የኬንያ እና የሩዋንዳ ጨዋታ ሲሆን የውድድሩ ጠንካራ ቡድን ኬንያ በመለያ ምት አሸንፋለች። በመደበኛው ሰዓት አንድ ለአንድ የተጠናቀቀው ጨዋታው ወደ መለያ ፍፁም ቅጣት ምት አምርቶ ኬንያ ሁለት ለአንድ አሸንፋለች።

ቀጥሎ 10:00 የተካሄደው እና በኢትዮጵያዊው ዋና ዳኛ ለሚ ንጉሴ የተመራው የዩጋንዳ እና የብሩንዲ ጨዋታ በዩጋንዳ ስድስት ለባዶ አሸናፊነት ተገባዷል።

ውድድሩ ዓርብ የሚጠናቀቅ ሲሆን የፍፃሜው ጨዋታም በዩጋንዳ እና ኬንያ መካከል ይደረጋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ