ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ ሰባት – ክፍል አምስት

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም በመሳጭ ትረካ ሀያ ዘጠነኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። ብራዚል ላይ ባተኮረው 7ኛ ምዕራፍ የክፍል አምስት መሰናዶን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።


እንግሊዞች በትልልቅ ዓለም አቀፍ የእግርኳስ  ውድድሮች ለሚገጥማቸው የውጤት ማጣት ተጫዋቾቻቸው በቴክኒክ አቅም የበቁ አለመሆናቸውን (Technical Inadequacy) በሰበብነት እንደሚያነሱ ሁሉ ብራዚሎችም በመከላከል የጨዋታ ሒደት ለሚያሳዩት ድክመት (Defensive Fraility) የአጨዋወት ሥርዓታቸውን ይተቻሉ፡፡ የፔርዲጋኦ <ጎተርዳመረንግ> (Gotterdamerung) ማመሳከሪያ ቀደም ሲል እንግሊዝ በሃንጋሪ በሜዳዋ 6-3 ከተሸነፈች በኋላ (Twilight of the Gods) ወይም “የአማልክቱ መጨረሻ” የሚል አርዕስት ይዞ የወጣውን የ<ሚረር> ጋዜጣ ሐሳብ የሚያስተጋባ አገለለጽ ነበር፡፡ ይህ ቁጭት የመነጨው ተመሳሳይ መነሻ ላይ ተመስርቶ እንጂ በተራ የሁኔታዎች መገጣጠም ሊሆን አይችልም፡፡ የውጤት ቀውሱን ዙሪያ-ገባ ላጤነ ያልተጠበቁ ሽንፈቶች እየተለመዱ መምጣታቸውን ከመቃወም የመጣ ማማረርም ይመስላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባህላዊው የአጨዋወት መንገድ ብቻ “ብቸኛውና የላቀው ስልት” ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት የሚያስገነዝብ ቁጣ አዘል መልዕክትም ተንጸባርቆበታል፡፡ ይሁን እንጂ የብራዚሎች ልማድ እና የእንግሊዞቹ ባህል ለየቅል መሆናቸው ጉዳዩን ምፀታዊ ይዘት እንዲኖረው አድርጎታል፡፡ ትክክለኛ የሚባል የአጨዋወት መንገድ የለም፤ አልፎ አልፎ ሁሉም የእግርኳስ አቀራረብ የያዘው ጥንካሬ አጠራጣሪ ሆኖ ይገኛል፤ ሌሎች ቦታዎች እንደ አዲስ ከሚፈጠሩት አንጻርም ያረጀና ያፈጀ መስሎ የመታየት ጋሬጣ ይገጥመዋል፡፡

ብራዚል በ1950ው የዓለም ዋንጫ በስድስት ጨዋታዎች ሃያ ሁለት ግቦች ብታስቆጥርም በፍጻሜው የገቡባት ሁለት ጎሎች ከሁሉም በላይ ጠቀሜታ ነበራቸው፡፡ ከዚህ ውድድር በኋላ የሃገሪቱ እግርኳስ ተንታኞች የብሄራዊ ቡድኑ የተከላካይ መስመር መጠናከር እንዳለበት በግልጽ አሳወቁ፡፡ በ1954ቱ ዓለም ዋንጫ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ የሚያተኩረው ፍላቪዮ ኮስታ ከመንበሩ ተነሳ፤ በመከላከል ሒደት ጥንቁቅ የነበረው ዜዜ ሞሬይራ መንበሩን ተረከበ፡፡ የአሰልጣኝ ለውጡን አስመልክቶ ስሙ ያልተጠቀሰ ፈረንሳዊ ጋዜጠኛ ” አንድ አርጀንቲናዊ የሙዚቃ ተወዛዋዥን በእንግሊዛዊ ካህን የመተካት ያህል ነው፡፡” ሲል ንጽጽሩን አስቀመጠ፡፡

በሲውዘርላንዱ የዓለም ዋንጫ የብራዚል ሶስቱ አስፈሪ የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside-Forwards) ጥምረት ፈረሰ፤ ከዩቬናል በተለየ ለመከላከል አደረጃጀቱ ጥንካሬ ተስማሚ የሆነና አመዛኙን የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቆሞ የሚጫወት የመሃል-ተከላካይ አማካይ (Stopper Centre-Half) የሆነው ፒንሄይሮ በቡድኑ ተካተተ፡፡ ብራዚል ሜክሲኮን በጥሩ ብቃት አሸነፈች፤ በቀጣዩ ጨዋታ ከዩጎዝላቪያ አቻ ተለያየች፤ በሩብ ፍጻሜው ከሃንጋሪ ጋር እህል አስጨራሽ ትግል ጠበቃት፤ የ<በርኑ ጦርነት> በሚል በሚታወቀው ጨዋታ 4-2 ተረታች፤ ብራዚል አሁንም ድል ተነሳች፡፡ የሃገሪቱ ልዑካን ቡድን መሪ የነበረው ጃኦ ሊይራ ፊልሆ በውድድሩ ዙሪያ ሰርቶት ይፋ ባወጣው ዘገባ ላይ “አብረቅራቂዎቹ ተጫዋቾቻችን በጨዋታው ጥበባዊ አቀራረብን ትተው ውጤት ላይ ብቻ የተመሰረተ አጨዋወት አሳዩ፡፡” በማለት በተለይ ጥቁሮቹ ተጫዋቾች ላይ ወቀሳ አቀረበ፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ አስተያየቱን ከቁብ የቆጠረው አልነበረም፤ እንዲያውም የእርሱ ነቀፌታ ችላ ተባለ፡፡ የጋሪንቻ ቅሬታ ግን ሁሉን የሚያስማማ ሆነ፤ በስትራተም ስሚዝ <ዘ-ብራዚል ቡክ ኦፍ ፉትቦል> የተለያዩ መጣጥፎች ስብስብ ውስጥ ” ሃገሪቱ የተጫዋቾችን የግል ክህሎት ወደጎን ብላ በሙሉ የቡድን ሥራ የአለም ዋንጫን ለማሸነፍ አቀደች፤ ስለዚህም ብራዚሎች ወደ አውሮፓ የተጓዙት ልክ እንደ አውሮፓውያኑ ለመጫወት አስበው ነበር፡፡ የብራዚላውያን እግርኳስ የእምነት መሰረት የተጣለው ግን በተጫዋቾቻችን የፈጠራ ክህሎት ላይ እንደነበር የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡” የሚል ሐሳብ አቀረበ፡፡ በውድድሩ ጋሪንቻ የታክቲክ አተገባበርን ሥርዓት ፍጹም ያለማክበር ባህሪ አሳይቷል፡፡ ይሁን እንጂ ድንገታዊው የፈጠራ ሒደት (Improvisation) እንዲያው ዝም ብሎ በግርግር በሚካሄደው ሩጫ ሊሳካ አልቻለም፡፡ ከዚያ ቀደም ቢጎዴ የተቸገረበት ደካማ የተከላካይ ክፍል ለተጋጣሚ ቡድን አጥቂዎች ሳይጋለጥ የተጫዋቾቹ የፈጠራ ክህሎት ውጤታማ ሊሆን የሚችልበት መዋቅር የግድ አስፈለገ፡፡ መፍትሄው ከ1950ዎቹ ጅምር ዓመታት አንስቶ በተለያዩ የልምምድ አይነቶች ሲፈለግ ሰንብቷል፡፡

<4-2-4 ፎርሜሽን> ማን ቀድሞ እንደፈጠረው አከራካሪ ነው፡፡ አሳፍ “ፎርሜሽኑ (4-2-4) ብዙ አባቶች አሉት፡፡” ይላል፡፡ ጥቂቶች ዜዜ ሞሬይራ የፎርሜሽኑ ቀዳሚ ተግባሪ እንደሆነ ይናገራሉ፤ ሌሎች ፍሌይታስ ሶሊች የ<4-2-4> ጀማሪ ስለመሆኑ ይከራከራሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ ይህን የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ማርቲም ፍራንቼስኮ እንዳመጣው ይሞግታሉ፡፡ ብዙዎች ግን የ<4-2-4> አሰላለፍ ትክክለኛ ቅርጹን ያገኘው በሳንቶስ ክለብ አሰልጣኝ ሉላ ከተጠቀመው በኋላ እንደነበር ይወተውታሉ፡፡ የአክሴል ቫርታኒያን መረጃ ተዓማኒ ከሆነ ደግሞ ይህ ፎርሜሽን ጭራሽ የብራዚላውያን ግኝት እንዳልሆነና ቦሪስ አርካዲዬቭ በዳይናሞ ሞስኮ ጥቅም ላይ ካዋላቸው በርካታ የአደራደር መዋቅሮች መካከል አንዱ እንደነበረ እንረዳለን፡፡ ከእነዚህ ውስብስብ የፎርሜሽን ባለቤትነት ንትርኮች ውጪ እርግጠኛው ጉዳይ ብራዚሎች በ<ዲያጎናል> ግኝታቸው፣ ሃንጋሪውያን ደግሞ ወደኋላ ያፈገፈገ የመሃል አጥቂ (Withdrawan Centre-Forward) በተጓዳኝም ከመሃለኛው የሜዳ ክፍል ለተከላካዮቹ የቀረበ የግራ መስመር አማካይ (Withdrawan Left-Half) ሚናዎች ፈጠራቸው ይታወቃሉ፡፡ ስለዚህ ሁለቱም ሃገራት ለየብቻቸው ባሻሻሉት የተጫዋቾች ሚና እና የመጫወቻ ስፍራዎች ሽግሽግ <4-2-4> የማይቀር እድገት ሊሆን እንደሚችል አመላክተዋል፡፡

ፓራጓዊው አሰልጣኝ ፍሌይታስ ሶሊች <4-2-4> ፎርሜሽንን በማስተዋወቅ ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ አሰልጣኙ ከ1953-1955 ድረስ በነበሩት ዓመታት ከፍላሚንጎ ጋር ሆኖ የካሪዮካ ግዛት ሶስት ዋንጫዎችን በተከታታይ ሲያሸንፍ የተጠቀመው <4-2-4>ን ነበር፡፡ ያም ሆኖ በጥልቀት ተዘጋጅቶበት ፎርሜሽኑን ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀመው ሰው ማርቲም ፍራንቼስኮ ይመስላል፡፡ ፍራንቼስኮ በወቅቱ ከቤሎ ሆሪዞንቴ ሃያ ማይሎች ርቀት ላይ ከምትገኘው ኖቫሊማ ከተማ <ቪላኖቫ> ክለብን ያሰለጥን ነበር፡፡ አሰልጣኙ ሊቶ የተባለውን የቡድኑ ግራ መስመር አማካይ (Left-Half) ወደኋላ ሳበውና እንደ “አራተኛ ተከላካይ” (Quarto Zagueiro/Forth-Defender) እንዲጫወት አደረገው፡፡ ስያሜው እስካሁንም ድረስ በብራዚል እግርኳስ ከተከላካይ ክፍሉ ተነጥሎ ወደፊት በመሄድ የአማካይ ክፍሉን የሚቀላቀል ተጫዋች ይጠራበታል፡፡ ግትሩን <4-2-4> በተመለከተ ከጅምሩ አንስቶ በሁለት ተጫዋቾች የተዋቀረ የመሃል ክፍል (Two-Man Midfield) በተጋጣሚ ቡድን የአማካይ ክፍል በቀላሉ ከፍተኛ ጫና ሊደርስበት እንደሚችልና ፈጣን ሽፋን ለመስጠት አዳጋች ሁኔታ እንደሚፈጠር በአግባቡ ይታወቅ ነበር፡፡ ስለዚህ ከአራቱ የፊት መስመር ተሰላፊዎች መካከል አንደኛው ወደኋላ የሚመለስበት ሥርዓት መዘርጋት ግዴታ ሆነ፡፡ በፍራንቼስኮ ቡድን የቀኝ መሥመር አማካዩ (Right-Winger) ኦሶሪዮ ነበር፡፡ በተግባራዊ እንቅስቃሴ ወቅት <4-2-4> ፎርሜሽን በዚህ ቅርጽ ሜዳ ላይ የሚታየው ለጥቂት ቅጽበቶች ብቻ ነው፡፡ በኳስ ቁጥጥር የበላይነት (Possession) ሲገኝ እና የማጥቃት ዑደቱ (Attacking Phase) ሲካሄድ <4-2-4> ወደ <3-3-4> ይቀየራል፤ ከኳስ ቁጥጥር ውጪ (Out of Possession) ሲኮን ደግሞ <4-3-3> ይሆናል፡፡ ይህ ፎርሜሽን ሰፊ ተቀባይነት አግኝቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁለት ተጨማሪ እድገቶች አሳይቷል፡፡

ምስል፦ 4-2-4; ቪላኖቫ; 1951

አንደኛው እድገት፦ ዜዜ ሞሬይራ በፍሎሚኔንሴ ክለብ ሳለ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈጠረውና ተጫዋቾች በሚጫወቱበት የሜዳ ክፍል ሆነው ቦታቸው በተጋጣሚ ቡድን ተጫዋቾች ቁጥጥር ሥር እንዳይሆን ክልላቸውን የሚጠብቁበት የመከላከል ዘዴ (Zonal-Marking System) ነበር፡፡ ይህ የመከላከል ጥበብ በሚዋልል እንቅስቃሴ ማራኪ የጨዋታ ፍሰትን (Fluidity) ከመፍቀዱ በተጨማሪ በW-M ፎርሜሽን በብዛት የሚተገበረውን ጥብቅ ተጫዋችን-በ-ተጫዋች የመከታተል ሥርዓት (Man-To-Man Marking) ገሸሽ እንዲል አድርጓል፡፡ በተለይ በ1950 ሰው-በ-ሰው የመያዝ ሲስተም አዋጭነቱን አጥቶ ነበር፡፡ በ1949 አርሰናሎች በብራዚል የጉብኝት ጉዞዎችን ሲያደርጉ በጨዋታ ወቅት አብዛኞቹ የሃገሪቱ ቡድኖች ከየትኛውም የመጫወቻ ክልል ለማጥቃት ባላቸው ፍላጎትና በሚያሳዩት ጥረት ተገርመዋል፡፡እንግሊዞቹ ይህንን የተጫዋቾች እንቅስቃሴ በተግባር ለማዋል ከመስጋት ባለፈ ለታክቲካዊ መርሆዎች ተገዢ ያለመሆን ድክመትም እንደሆነ ያስቡ ነበር፡፡ በጊዜው የአርሰናሉ መስመር ተከላካይ (Full-Back) ሎውሪ ስኮት ክለቡ በፍሎሚኔንሴ ላይ ስለተቀዳጀው የ5-1 ድል ” በድንገት አንድ ተጫዋች ይመጣና በከፍተኛ ፍጥነት ኳሷን ይዞ ይከንፋል፤ ወደ እኛ ግብ አቅጣጫ ጠንካራ ምት ይመታል፤ ኳሷ ወደ ጎሉ እያሰፋች ትምዘገዘጋለች፡፡ ከዚያም እኛ ለስህተቱ የሚወቀሰውን ሰው ፍለጋ እርስ በርሳችን እንተያያለን፤ ነገር ግን ማንም ተጠያቂ የሚሆንበትን ምክንያት እናጣለን፡፡ በመጨረሻ የገባን ነገር የመስመር ተካላካያቸው የማጥቃት ሒደቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳትፎ እንደነበረው ነው፡፡ አየህ! እነርሱ ጉዳያቸው አይደለም፤ እኔ’ኮ ወደ ተጋጣሚ የሜዳ ክልል ድርሽ ብዬ አላውቅም፡፡” ሲል ለአይዳን ሐሚልተን በሰጠው ቃለ-ምልልስ ገልጿል፡፡

ከዚያ በኋላ በብራዚላውያን የእግርኳስ ባህል የሚያጠቁ የመስመር ተከላካዮች (Attacking Full-Backs) እጅጉን ጠቃሚና ተፈላጊ እየሆኑ ሄዱ፡፡ ምንም እንኳ <4-2-4> ፎርሜሽን ከመስመር ተከላካዮቹ ፊትለፊት ሰፊ ክፍተት የሚፈጥር መዋቅር ቢሆንም ተጫዋቾቹ ይበልጥ ወደፊት ተጠግተው እንዲጫወቱ ያበረታታቸዋል፤ ለቡድን አጋሮቻቸውም አፋጣኝ ከለላ ወይም ሽፋን (Immediate Cover) እንዲሰጡ ያግዛል፡፡ ሰውን-በ-ሰው በመያዝ የመከላከል ሥርዓት (Man-To-Marking) ተግባር ላይ የመዋሉ ጉዳይ እያከተመ በመሄዱ በመስመር ተከላካይ (Full-Back) አማካኝነት እንዲከወን የሚጠበቀው የፊትለፊት እንቅስቃሴ (Forward Movement) ለአራተኛው ተከላካይ (Fourth Defender) ቀላል እየሆነለት መጣ፡፡ ተጫዋቹ ቦታውን ሲለቅ በW-M ፎርሜሽን የተከላካዮች አወቃቀር መሰረት በሚኖሩት ሌሎች ተጫዋቾች አማካኝነት የሶስት ተከላካዮች በቂ ሽፋን (Three-Man Defensive Cover) ስለሚያገኝ ከኋላው ስለሚተወው ሰፊ ቦታ ስጋት ሳይገባው ይህን ሚና መወጣት ቻለ፡፡

ሁለተኛው ግኝት፦ ደግሞ በተለምዶ የጨዋታ አቀጣጣይነት ተብሎ የሚታወቀው የአጥቂ አማካይነት ሚና (Ponta da lanca) ነው፡፡ ከሁለቱ የመሃል አጥቂዎች (Central-Forwards) አንደኛው ከተጣማሪው ጀርባ ጥቂት ወደኋላ ይሳብና የፊት መስመር ተሰላፊዎች ከአማካይ ክፍሉ ጋር ተገቢ ግንኙነት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ በእርግጥ ይህ የሜዳ ላይ ኃላፊነት ሙሉ በሙሉ አዲስ አልነበረም፡፡ በዲያጎናል ፎርሜሽን የማጥቃት ሒደቱን ከሚመራው የፊት መስመር ተሰላፊ (Attacking Inside-Forward) የሚለየው ተጨማሪ ሚናም አልያዘም ነበር፡፡ ፑሽካሽ በሃንጋሪ ብሄራዊ ቡድን ቆይታው ለበርካታ ዓመታት ተመሳሳዩን አጨዋወት ተግብሯል፡፡ ይሁን እንጂ በተደጋጋሚ የመለዋወጥ ባህሪ ለሚያሳየው የብራዚሎች እግርኳስ እጅጉን አመቺ የሆነ የሜዳ ክፍል (Position) ላይ የሚገኝ የተጫዋቾች ተፈጥሯዊ ጥበብ ማሳያ ይመስላል፡፡ ሚናው ወዲያውኑ ከ<ትሬስ ኮራኮኤስ> ከተማ በተገኘው ኮስማና ታዳጊ አማካኝነት ትልቅ ትኩረት አገኘ፡፡ ሉላ ለደቃቃው ተዓምረኛ ተጫዋች በሳንቶስ የመጀመሪያ ተሰላፊነት ዕድል ሲሰጠው ፔሌ ገና የአስራ ስድስት ዓመት ልጅ ነበር፡፡ ከዓመት በኋላ ሃገሪቱ ቀዳሚውን የአለም ዋንጫ ድሏን ስትቀዳጅ ፔሌ የቡድኑ አነሳሽ ሞተር ሆነ::

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም ዘጠኝ መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡