ድሬዳዋ ከተማዎች አራት ተጫዋቾች በማስፈረም ወደ ዝውውር ገበያው ገብተዋል

በያዝነው የዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾች ያጡት እና እስካሁን ተጫዋቾች ሳያስፈርሙ የቆዩት ብርቱካናማዎቹ አራት ተጫዋቾችን በማስፈረም ወደ ገበያው ገብተዋል።

ዋለልኝ ገብሬ የመጀመርያው ፈራሚ ነው። የእግር ኳስ ህይወቱን በቅዱስ ጊዮርጊስ ታዳጊ ቡድን ጀምሮ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ኤሌክትሪክ እና ወልዋሎ የተጫወተው ይህ አማካይ ከስድስት ወር የጅማ አባጅፋር ቆይታ በኃላ ነው ድሬዳዋ ከተማን የተቀላቀለው።

አማኑኤል ተሾመ የምስራቁን ክለብ የተቀላቀለ ሌላኛው ተጫዋች ሆኗል፡፡ የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ እና ወላይታ ድቻ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ያለፉትን ሁለት ዓመታት በመከላከያ ያሳለፈ ሲሆን የቡድኑ ሁለተኛ አዲስ አማካይ ፈራሚ ሆኗል፡፡

ሌላኛው ፈራሚ ዘሪሁን አንሼቦ ነው። ዘንድሮ ከሊጉ በተሰናበተው ደቡብ ፖሊስ በግሉ ጥሩ ጊዜ ያሳለፈው የቀድሞው የመተሐራ የመሀል እና የቀኝ መስመር ተከላካይ ከአንድ ዓመት የፖሊስ ቆይታ በኋላ ወደ ቀድሞ ክለቡ ድሬዳዋ በድጋሚ በአንድ ዓመት ውል ተጉዟል፡፡

የክለቡ አራተኛ ፈራሚ ደግሞ ዘካሪያስ ቱጂ ሆኗል፡፡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የተገኘው የግራ መስመር ተከላካዩ በ2010 ወደ ኤሌክትሪክ ቢያመራም ከክለቡ ጋር ያለመግባባት ፈጥሮ በመለያየቱ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት ያለ ክለብ አሳልፏል። ተጫዋቹ በቅርቡ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበረው ቆይታ ከእግርኳስ በመራቁ የተሰማውን ከባድ ስሜት ገልጾ አቋሙን ለመጠበቅ በግሉ ልምምድ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፆ ነበር።

በቴዎድሮስ ታከለ እና ማቲያስ ኃይለማርያም


© ሶከር ኢትዮጵያ