ሪፖርት| የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሜዳው አቻ ተለያይቷል

ለ2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታውን በሜዳው ከሌሶቶ ጋር ያከናወነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን 0-0 ተለያይቷል።

በግሩም የደጋፊ ድባብ ታጅቦ በባህር ዳር ስታዲየም የተከናወነው ጨዋታው ምንም የተሻለ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ሳይስተዋልበት ተጠናቋል። በ4-3-3 የተጨዋች አደራደር ቅርፅ ወደ ሜዳ የገቡት ዋሊያዎቹ ኳስን በመቆጣጠር ረገድ የተሻለ ቢመስሉም የጠራ የግብ ማግባት እድሎችን በመፍጠር በኩል ግን ተዳክመው ታይተዋል። በተቃራኒው በ4-2-3-1 አስተላለፍ ወደ ሜዳ የገቡት ተጋባዦቹ ሌሴቶዎች ግብ እንዳይቆጠርባቸው በጥንቃቄ ለመጫወት ጥረት አድርገዋል።

ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ኳስ ተቆጣጥረው ሲንቀሳቀሱ የተስተዋሉት የአሰልጣኝ አብርሃም ተጨዋቾች ጨዋታው እንደተጀመረ በዑመድ ኡኩሪ እና ያሬድ ባዬ አማካኝነት ሙከራ ሰንዝረው ነበር። በተደጋጋሚ የመዓዘን ምቶችን አግኝተው የግብ እድል ቢፈጥሩም አጋጣሚውን ወደ ግብነት ሳይቀይሩ ቀርተዋል። ከዚህ በተጨማሪ በ10ኛው ደቂቃ ሽመልስ በቀለ ለአማኑኤል ገ/ሚካኤል ጥሩ ኳስ አቀብሎት በተፈጠረ እድል ዋሊያዎቹ ወደ ግብ ቀርበው ነበር። ከደቂቃ በኋላ ቢኒያም በላይ ለአማኑኤል ገ/ሚካኤል ረጅም ኳስ ልኮለት አማኑኤል ግብ አስቆጥሮ የለቱ ዳኛ ከጨዋታ ውጪ በማለት ግቡ ሳይፀድቅ ቀርቷል።

ወደ ግብ ክልላቸው ተጠግተው በጥንቃቄ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሌሶቶዎች የመጀመሪያ ሙከራቸውን በ15ኛ ደቂቃ ሰንዝረው ጀማል ጣሰው አምክኖባቸዋል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ዳግም በቀኝ መስመር በተነሳ የመልስ ውርወራ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል የደረሱት ሌሴቶዎች በጃንግ ታባንትሶ አማካኝነት በግምባር ሙከራ ሰንዝረው መክኖባቸዋል።

በአስገራሚ የራስ መተማመን ሲጫወቱ ከነበሩት የመሃል ተከላካዮቹ (አስቻለው እና ያሬድ) ጀምሮ ኳስ በመመስረት ወደ ፊት ለመሄድ ሲሞክሩ የነበሩት ዋሊያዎቹ የሌሶቶን የተከላካይ ክፍል ማስከፈት ተስኗቸው ጨዋታው ቀጥሎ በ23ኛው ደቂቃ ሽመልስ በቀለ በረጅሙ የተላከለትን ኳስ በሚገባ ተቆጣጥሮ ለአህመድ ረሺድ ሰቶት አህመድ በሞከረው ሙከራ ዋሊያዎቹ ወደ ግብ ደርሰው ነበር። ከሁለት ደቂቃ በኋላም ዳግም በመልሶ ማጥቃት ሽመልስ ወደ ሌሴቶ የግብ ክልል ደርሶ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ቢያደርግም ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውበታል።

የሚያገኙዋቸውን የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች በአግባቡ ለመጠቀም ሲጥሩ የተስተዋሉት ሌሴቶዎች በ32ኛው ደቂቃ በሴትሩማኔ አማካኝነት ጥሩ ሙከራ ሰንዝረው ነበር። ከደቂቃ በኋላ ለተሰነዘረባቸው ያልታሰበ ጥቃት ምላሽ ለመስጠት ያሰቡ የሚመስሉት ዋሊያዎቹ አማኑኤል ለሙጂብ ባመቻቸለት ኳስ አማካኝነት እጅጉን ለግብ ቀርበው ነበር።

ከ35ኛው ደቂቃ በኋላ አሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የአማኑኤልን እና ዑመድን ቦታ ቀያይረው የፊት መስመራቸውን ለማስተካከል ሞክረዋል። በዚህም አማኑኤል መጀመሪያ ተሰልፎበት ከነበረበት ቦታ በተሻለ ለመንቀሳቀስ ሞክሮ ግብ ለማስቆጠር ጥሯል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ አራት ደቂቃ ሲቀረው የቀኝ መስመር ተከላካዩ አህመድ ረሺድ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ አወጣለው ብሎ ተጨርፎበት ራሱ ላይ ለማስቆጠር ተቃርቦ የግቡ ቋሚ መልሶታል። የመጀመሪያው አጋማሽም ግብ ሳይቆጠርበት 0-0 ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ሁለቱም ቡድኖች ከመጀመሪያው አጋማሽ የተለየ አቀራረብ ሳያስመለክቱ ጨዋታው ሲቀጥል በአንፃራዊነት ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የተንቀሳቀሱት ሌሶቶዎች ጥንቃቄ የታከለበት የጨዋታ ስልት ተከትለው ተንቀሳቅሰዋል። ዋሊያዎቹ በአንፃሩ ከመጀመሪያው አጋማሽ በቁጥር ያነሰ የግብ ማግባት ሙከራ በማድረግ የተቀዛቀዘ ጨዋታ አስመልክተዋል።

በ50ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም ለአህመድ ረሺድ የአየር ላይ ኳስ ልኮለት አህመድ ያልተጠቀመበት ኳስ የዋሊያዎቹ የመጀመሪያ የሁለተኛ አጋማሽ ሙከራ ነበር። ያሬድ እና አስቻለውን ወደ መሃል ገፍተው ሲጫወቱ የነበሩት አሰልጣኝ አብርሃም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ኳስ ለመቆጣጠር ብቻ ኳስ ተቆጣጥረው ሲንቀሳቀሱ ተጋጣሚያቸው ደግሞ ረጃጅም ኳሶችን በመጠቀም ወደ ግብ ለመድረስ ሞክረዋል። የአማካይ እና የአጥቂ ክፍላቸውን ለማደስ ያሰቡት አሰልጣኝ አብርሃም አዲስ ግዳይ እና ከነዓን ማርክነህን ለውጠው በማስገባት ይበልጥ ማጥቃቱ ላይ አትኩሮት ሰጥተዋል። ምንም እንኳን የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጨዋቾች ወደ ሜዳ ቢገቡም ዋሊያዎቹ የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ ግን ተስኗቸዋል።

አዲስ ከገባ በኋላ በ3 ተከላካይ ለመጫወት የወደዱት ዋሊያዎቹ በአንፃራዊነት ከሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በተሻለ ተንቀሳቅሰዋል። ከአዲስ እና ከነዓን በተጨማሪ ተቀይሮ የገባው ተስፈኛው ወጣት መስፍን ታፈሰ የዋሊያዎቹን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማፍጠን ጥሮ በግሉ ሙከራዎችን ሲያደርግ ታይቷል። ሆኖም የሁለተኛው አጋማሽም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ሳያስተናግድ ያለግብ ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ዋሊያዎቹ ወደ 2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚያደርጉትን ጉዞ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። የመልሱ ጨዋታ ጳጉሜ 3 (እሁድ) ሌሶቶ ላይ ሲደረግ ኢትዮጵያ በድምር ውጤት የሚያሳልፋትን ውጤት ካገኘች ወደ ምድብ ማጣርያ የምታልፍ ይሆናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ