ከፍተኛ ሊግ | ጌዲኦ ዲላ አራት ተጨማሪ ተጫዋቾች አስፈረመ

አሰልጣኝ ደረጀ በላይን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠረውና ሦስት ተጫዋቾች አስፈርሞ የነበረው ጌዲኦ ዲላ አራት አዳዲስ ተጫዎቾች ወደ ቡድኑ ቀላቅሏል።

ወልዳይ ገ/ሥላሴ ለዲላ ከፈረሙት መካከል ነው። አማካዩ ከዚህ ቀደም በወሎ ኮምቦልቻ፣ አውስኮድ፣ ወልዲያ እና መቐለ የተጫወተ ሲሆን ወደ ፕሪምየር ሊግ ያደገው ወልቂጤ ቡድን ውስጥ በአሰልጣኝ ደረጀ በላይ ስር ተጫውቷል ።

ደረሰ ተሰማ ሌላው ተጫዋች ነው። የተከላካይ አማካይ ተጫዋች የሆነው ደረሰ በአርሲ ነገሌ እና በቡሌ ሆራ የተጫወተ ሲሆን ይህን የውድድር ዓመት በሀላባ ከተማ ነበር ያሳለፈው።

ክንዴ አቡቹ ሌላው አዲስ ፈራሚ ነው። የቀድሞው የባቱ ከተማ አጥቂ በቡታጅራ ያለፉትን ሁለት ዓመታት ሲጫወት የቆየ ሲሆን በከፍተኛ ሊጉም ለኮከብ ጎል አስቀሰጣሪነት እስከመጨረሻው ሳምንት ድረስ ሲፎካከር ቆይቷል።

በተከላካይ ስፍራ ላይ የሚጫወተው አምሳሉ መንገሻ አራተኛው አዲስ ፈራሚ ሆኗል። አምሳሉ ነቀምት ከተማ በከፍተኛ ሊጉ መሳተፍ ሲጀምር አብሮ የነበረ እንዲሁም በ2010 በሀምበሪቾ ያሳለፈ ተጫዋች ሲሆን በ2011 ወደ ነቀምት ከተማ ተመልሶ ቡድኑን በአምበልነት መምራት ችሏል።


© ሶከር ኢትዮጵያ