ቅዱስ ጊዮርጊስ አዲስ አሰልጣኝ ቀጥሯል (ዝርዝር ዘገባ)

ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማኅበር በዛሬው ዕለት ባልተጠበቀ መልኩ ሰርቢያዊው የ47 ዓመት ጎልማሳ ሰርዳን ዚቮጅሆቭ (ሰርጂዮ) በአሰልጣኝነት ዛሬ ከሰዓት በሸራተን ሆቴል ለመገናኛ ብዙሃን አስተዋውቋል፡፡

በክለቡ ስራ አስኪያጅ በሆኑት አቶ ሰለሞን በቀለ የመክፈቻ ንግግር የተጀመረው መርሃ ግብሩ በመቀጠልም የክለቡ የበላይ ጠባቂ አቶ አብነት ገ/መስቀል ስለ አዲሱ አሰልጣኝ መጠነኛ ገለፃን ሰጥተዋል፡፡ በገለፃቸው አዲሱ አሰልጣኝ ሰርዳን ዚቮጅሆቭ (ሰርጂዮ) በሀገራቸው በከፍተኛ ደረጃ እግርኳስን ለ15 ዓመታት የተጫወቱ እና ለ16 ዓመታት በቆየው የስልጠና ህይወታቸውም ከኤሺያ እስከ አፍሪካ በተለያዩ ክለቦች ስለማሰልጠናቸው ገልፀዋል። በአፍሪካ በነበራቸው ቆይታም በተለይ በምስራቅ አፍሪካ በታንዛኒያና ዩጋንዳ የሚገኙ ኃያላን ክለቦችን ስለማሰልጠናቸውም ገልፀዋል፡፡

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ለመቆየት የተፈራረሙት አሰልጣኝ ሰርጂዮ ከነገው ዕለት ጀምሮ በቀጥታ ወደ ስራ የሚገቡ ሲሆን ከዚህ ቀደም በአሰልጣኝ ቡድን ውስጥ የነበሩት ምክትል አሰልጣኙ ዘሪሁን ሸንገታና ካሜሩናዊዉ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ኒዲዬ በሥራቸው የሚቀጥሉ መሆናቸውንም አያያይዘው አቶ አብነት ገ/መስቀል ገልፀዋል፡፡

በማስከተልም ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርጂዮ አጠር ያለ ንግግርን አድርገዋል። የክለቡ ቦርድ አመራሮች ይህንን ጠንካራና ታላቅ ክለብ በአሰልጣኝነት እንዲመሩ መምረጣቸው የፈጠረባቸውን ደስታ ገልፀው፤ ይህንን ቡድን ውጤታማ ለማድረግ ጠንክረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡

በማስከተልም በስፍራው ከተገኙ የመገናኛ ብዙሃን አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች አቶ አብነትና አሰልጣኝ ሰርጂዬ ምላሽ ሰጥተዋል፤ ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጡትን ምላሾችም እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

አሰልጣኝ ሰርጂዮ

ስለሚከተሉት የጨዋታ ፍልስፍና

“እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓይነት ሁሉንም ዋንጫ የማሸነፍ ፍላጎቱ ከፍተኛ የሆነ ክለብ ሁሉንም ጨዋታ የሚያደርገው ለማሸነፍ ብቻ ነው። ሁሉንም ጨዋታ ለማሸነፍ ደግሞ አጥቅቶ መጫወት የግድ ይላል፡፡ አሁን ላይ ሆኜ መናገር የምችለው ነገር ቢሆን ተመልካች ወደ ሜዳ የሚገባው ማራኪ ጨዋታና ቡድኖች ሲሸናነፉ ለማየት ነው። ማንም ተመልካች ቢሆን ሜዳ ገብቶ 0-0 የሚጠናቀቁ ጨዋታዎችን መመልከት አይፈልግም። ስለዚህ አጥቅቶ የሚጫወት ቡድንን ለመገንባት እንጥራለን። በተረፈ ያሉኝን ተጫዋቾች ሳልመለከት ስለ ታክቲክና ተያያዥ ጉዳዮች ማውራትን አልፈልግም፡፡”

ቡድኑ ባለፋት ሁለት ዓመታት ከዋንጫ መራቁ ሥራቸው ላይ ተጨማሪ ጫና ስለመፍጠሩ

“እኔ በባህሪዬ ከባድ ፈተናዎችን መጋፈጥ የምወድ ሰው ነኝ፤ ስለዚህም ነው ይህን ሥራ የተረከብኩት፡፡ ቡድኑ ላለፋት ሁለት ዓመታት ዋንጫ ስላለማንሳቱ መረጃ አለኝ። ነገርግን በሁሉም በሄድኩባቸው ሀገራት መስራት የምፈልገው ቡድን በመሰረታዊነት እንደ ጀርመኖች ጠንካራ ዲሲፕሊን ያለው፣ እንደ ስፔን ቡድኖች ጥሩ የፈጠራ ብቃት እንዲሁም እንደ ብራዚሎች ስል የአጥቂ መስመርን መገንባት መቻላችን ነው ወሳኙ። ከዛም የምንፈልገውን ግብ ማሳካት አይሳነንም፡፡”

አቶ አብነት ገ/መስቀል

በቀጣይ ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ ስለሚሳተፍበት ውድድር

“በቅድሚያ ሊሰመርበት የሚገባው ጉዳይ በየትኛው ውድድር ብንካፈል እኛ እንደ ጊዮርጊስ ያለን አቋም በተካፈልንበት ውድድር ሁሉ ጠንካራ ሆኖ በመቅረብ የበላይ ሆኖ መገኘት ነው፡፡ የእኛ አቋም አሁንም ቢሆን ለሀገሪቱ እግርኳስ አዋጭ በሆነው ውድድር ላይ መካፈል ነው፤ እኛ አሁንም የምንጠብቀው መንግስት የሚሰጠንን መልስ እንጂ እኛ ከሌሎች የአዲስአበባ ክለቦችና ሌሎች አጋር ክለቦች ጋር በመሆን የአዲስአበባ ሊግን ለመመስረት ቁርጠኛ አቋም ይዘናል። የአዲስአበባ ሻንፒዮና ለመመስረት ከዚህ ቀደም የነበሩ ደንቦች ከመደርደሪያ አውርዶ አቧራቸውን በማረገፍ እውን ማድረግ የሚቻል ነገር ነው። ስለዚህ መንግስት አሁንም ቢሆን ለሀገሪቱ እንደአጠቃላይ የሚበጃትን ነገር ከግምት በማስገባት ውሳኔ ይሰጠናል ብለን እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡”

ስለ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ

“በክረምቱ የክለባችን ስም ከርካታ አሰልጣኞች ጋር ሲያያዝ ሰንብቷል ፤ የውጭ ሀገር አሰልጣኝ እየፈለግን በነበረብንበት ወቅት ከአሰልጣኝ ውበቱ ጋር ተገናኝተን በግል ቅድመ ስምምነት ፈፅመን ነበር። ነገርግን በሂደት በእኛ እምነት የተሻለ አማራጭ ስናገኝ የተሻለ ብለን ያመነውን ወስነናል። ስለዚህ በይፋ እስካልተፈራረምን ድረስ ከየትኛውም አሰልጣኝ ጋር መስማማት ይቻላል ከውበቱ ጋርም የሆነው ይህ ነው፡፡”

አሰልጣኙ ከመምጣቱ በፊት ስለፈረሙ ተጫዋቾች

“ደካማ በሆነው ሊጋችን ውስጥ በዓመት ውስጥ ከአምስት ያላነሱ ጎልተው የሚወጡ ተጫዋቾች ሊኖሩ ይችላሉ። እኛ እንደጊዮርጊስ የተጫዋቾች ምልመላ በዘፈቀደ የሚከወን ጉዳይ አይደለም፤ በሂደትና በከፍተኛ ዝግጅት እንጂ። ወደ ቡድናችን የመጡት ተጫዋቾች ዓመቱን ሙሉ በክለባችን ሰዎች የነበራቸው እንቅስቃሴ ከግምት በማስገባት በጥንቃቄ የተመለመሉ ናቸው። እነዚህም ለአሰልጣኙ ጠቃሚ ግብዓት እንደሚሆኑ ሙሉ እምነት አለን፡፡ ከዚህ ቀደም እናደርገው እንደነበረው በክለባችን ያለውን ቀሪ 2 (3) የውጭ ሀገራት ተጫዋቾች ኮታ አዲስ በሚመጣው አሰልጣኝ የታመነባቸው ተጫዋቾች እንዲፈርሙ እናደርጋለን፡፡”

ስለተጫዋቾች የደሞዝ ጣርያ

“ተጫዋቾች በፈለጉት የደሞዝ መጠን ተደራድረው መጫወት እንዳለባቸው እናምናለን፤ በነፃ ገበያ በምትመራ ሀገር ውስጥ 50 ሺህ ብር ከፍተኛ ብሎ ጣርያ ማስቀመጡ በጣም የሚያሳዝንና የግፍም ግፍ ነው፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተጫዋቾቹ ደሞዝ ላይ ለመንግስት 7 ሚልየን ብር ገቢ አድርጓል። ይህም አሁን ተግባራዊ በሆነው ጣራ ቢሆን ወደ 3 ሚልየን ዝቅ ይል ነበር። ስለዚህ ይህ በዘፈቀደ የተወሰነ ውሳኔ ስለሆነ ዳግም ሊጤን ይገባዋል፡፡”

በስተመጨረሻም አሰልጣኙ በይፋ ከአቶ አብነት ጋር በመሆን የሁለት ዓመት ውል የተፈራረሙ ሲሆን በጋራ በመሆንም የፎቶ መርሃግብር ከውነው መርሐግብሩ ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ