ሴቶች ዝውውር | መቐለ 70 እንደርታ በርካታ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የነባሮቹን ውል አድሷል

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን በሴቶች ሁለተኛ ዲቪዚዮን ተሳታፊ በሆነበት በመጀመሪያው ዓመት ቻምፒዮኑ አቃቂ ቃሊቲን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው መቐለ 70 እንደርታ ስምንት ተጫዋቾች በማስፈም የአስራ አምስት ተጫዋቾችን ውል አድሷል።

በቀጣዩ የውድድር ዘመን በአንደኛ ዲቪዝዮን የሚወዳደረው መቐለ 70 እንደርታ ተፎካካሪ ቡድን ለመገንባት የአሰልጣኝ ህይወት አረፋይኔን ውል ከማደስ ጀምሮ ከግማሽ በላይ ነባሮችን ውል ማራዘም እና የሊጉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችን ማስፈረም ችሏል።

ክለቡ አዲስ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል ልምድ ያላቸው አማካይዋ ቅድስት ቦጋለ (አዲስ አበባ ከተማ – ፎቶ)፣ ግብ ጠባቂዋ ፍሬወይኒ ገብሩ (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ) እንዲሁም አጥቂዎቹ ትደግ ፍሰሀ እና አስካለ ገ/ፃዲቅ (አአ ከተማ) ሲጠቀሱ አጥቂዋ ሰሎሜ ጋይም (ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ተከላካዮቹ ሰላም ለዓከ (አአ ከተማ) እና ሙሉ በሪሁን (ልደታ) ሌሎች ቡድኑን የተቀላቀሉ አዳዲስ ተጫዋቾች ናቸው። ክለቡ በተጨማሪም ዘንድሮ የአዲስ አበባ ከተማ ረዳት አሰልጣኝ የነበረችው ፍሬ ገ/ሚካኤልን ወደ ተጫዋችነት በመመለስ ማስፈረምም ችሏል።

ክለቡ ወደ አንደኛ ዲቪዝዮን እንዲያድግ ወሳኝ ሚና የተወጡ አስራ አምስት ነባር ተጫዋቾች ኮንትራት ያራዘሙ ሲሆን ርሻን ብርሀኑ፣ ፍሬ አበራ፣ ዮርዳኖስ በርኸ፣ ዮርዳኖስ ምዑዝ፣ ሊዲያ ልዑል፣ ሸዊት አብርሀ፣ ሠላም ተክላይ፣ አበባ ገ/መድህን፣ ገነት ኃይሉ፣ ህይወት ኪሮስ፣ ፍፁም ኪሮስ፣ ፍረወይኒ ገ/ዮሐንስ፣ ምብራቅ አባዲ፣ ሳሮን ሰመረ እና አሰፈ አድሓኖም ለአንድ እና ሁለት ዓመታት በመቐለ ቆይታን የሚያደርጉ ተጫዋቾች ሆነዋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ