የሊግ አክስዮን ማኅበር ሊመሰረት ነው

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለዓመታት እፈፅመዋለው እያለ በተለያዩ ምክንያቶች ሳያሳካ የቀረው የሊግ አክስዮን ማኅበር ምስረታን መስከረም ወር ላይ ሊያደርግ ነው።

በተለያዩ መድረኮች ፌዴሬሽኑ ያስጠናውን ጥናት ካጠናቀቀ በኋላ ለክለቦች ሀሳቡን ቢያቀርብም እስካሁን ምላሽ ሳያገኝ የቀረው ይህ የሊግ ምስረታ መስከረም 12 (የቀን ለውጥ ሊደረግ ይችላል) ሁሉም የፕሪምየር ሊግ ክለቦች (24 ክለቦች) በተገኙበት ይፋ ለማድረግ ቀጠሮ በመያዝ ለክለቦቹ ደብዳቤ እየበተነ ይገኛል።

እንደ ፌዴሬሽኑ ሀሳብ ከሆነ በዕለቱ የሊግ አክስዮን ማኅበሩ መመስረት ይሁንታ ካገኘ በዕለቱ የሥራ አስፈፃሚ እና የተለያዩ የንዑሳን ኮሚቴ ከፍተኛ አመራሮችን ምርጫ በማድረግ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ለዓመታት እያወዛገበ እዚህ የደረሰው የሊግ አክስዮን ማኅበር ምስረታ ጉዳይ እንደሌሎች የፌዴሬሽኑ ውሳኔዎች ሁሉ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቶለት በሒደት ከመተግበር ይልቅ በአንድ ቀን ስብሰባ ሊመሰረት መቃረቡ የመስከረም 12 ስብሰባን አጓጊ መልክ ሰጥቶታል።


© ሶከር ኢትዮጵያ