ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ምዕራፍ ሰባት – ክፍል ስድስት

የጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም በግሩም አተራረክ ሠላሳኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። የመጽሐፉ 7ኛ ምዕራፍ በብራዚል ላይ ያተኮረ ሲሆን በዛሬው መሠናዶም ለምዕራፉ የመጨረሻ የሆነው ክፍል ስድስትን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።


ቤላ ጉትማን በኅዳር ወር 1956 ኻኖቭድን ይዞ የብራዚልን ምድር ከረገጠ በኋላ ያነሳቸው ቅሬታዎች እንዳሉ ሆነው በወቅቱ ክለቡ የተጠቀመበት የአጨዋወት ስልት በመላ ሀገሪቱ አግራሞት መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ያኔ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚተገበረው የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ተመሳሳይነት ግልጽ የነበረ ቢሆንም ብራዚሎች ከሃንጋሪዎች ቀደም ብለው ወደ 4-2-4 አምርተዋል፡፡ “በመሰረቱ በብራዚሎች እና በሃንጋሪዎች የ4-2-4 ፎርሜሽን አተረጓጎም መካከል የነበረው ልዩነት ወደ መሐለኛው የሜዳ ክፍል አፈግፍጎ የሚጫወተው የፊት መስመር ተሰላፊ የሚለብሰው የመለያ ቁጥር ላይ ነበር፡፡ በ1958 ብራዚሎች ለዚህ ሚና ከመሐል አጥቂው በስተቀኝ የሚጫወተው የፊት መስመር ኮከብ (Inside-Right) ዲዲን መረጡ፤ ሃንጋሪዎች ደግሞ ዋነኛውን የመሃል አጥቂ (Centre-Forward) ወደኋላ እንዲሳብ አደረጉ።”

በፎርሜሽኑ አተገባበር ዙሪያ ሁለቱም ብሔራዊ ቡድኖች መጠነኛ ተመሳስሎዎችን አሳይተዋል፡፡ በሁለቱም ቡድኖች ወደኋላ ያፈገፈገው አጥቂ (Withdrawn Forward) በመሃለኛው ክፍል ወደ ግራው መስመር አጋድሎ ይንቀሳቀሳል፤ የግራ መስመር አማካዩም (Left-Half) ይበልጥ የመከላከል ኃላፊነት ለመወጣት ከነበረበት ቦታ ትንሽ ርቀት ወደኋላ ይሳባል፤ የቀኝ መስመር አማካዩ (Right-Half) ደግሞ በክፍት የማጥቃት ሒደቱ ላይ በመሳተፍ የመሃሉን ከፍል ሚዛን ለመጠበቅ ይጥራል፡፡” ብሏል ናንዶር ኼጁኩቲ የሁለቱን ሃገራት የ4-2-4 ፎርሜሽን አጠቃቀምን በተመለከተ በሰጠው አስተያየት፡፡ 

በብራዚል የጉትማን ተጽዕኖ ከአጨዋወት ሥርዓት (System) ይልቅ በዘይቤ (Style) ላይ ያመዝን ነበር፡፡ እዚህ ጋር ቀጥተኛነት (Orthodoxy) በተለይም ብሪታኒያውያን ስለ ታላቁ የሃንጋሪ ብሄራዊ ቡድን የያዙትና ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው ቀጥተኛ የእግርኳስ አቀራረብ ምልከታቸው (British Orthodoxy) መልክ መያዝ ነበረበት፡፡ እንግሊዛውያን ተመልካቾች በአራኒክሳፓት ቡድን ተጫዋቾች (Aranycsapat) የቴክኒክ ችሎታ እንዲሁም ወደኋላ ባፈገፈገ ሚና እየተንቀሳቀሰ አጠቃላይ የጨዋታውን ፍሰት በሚያሳልጠው አጥቂ ሐሳባቸው ተወስዶ ነበር፡፡ ምናልባት ለዓመል ያህል በመጠኑ ይለያዩ ይሆናል እንጂ የሃንጋሪያውያኑ <አራኒክሳፓት> ከኦስትሪያኖቹ የ<ዉንደርቲም> አቀራረብ ብዙም አይራራቅም፤ መሰረታዊ የሆነ ልዩነትም አልታየባቸውም፡፡ እንዲያም ሆኖ ሃንጋሪዎች ጥረታቸውን ከግብ ለማድረስ ከፍተኛ ፍጥነት ነበራቸው፡፡ ጥበበኝነታቸውንም በቀጥታ ዋነኛ ትልማቸው ወደ ሆነው አሸናፊነት የሚያመሩበት መሻገሪያ አድርገው ይቆጥሩታል፡፡ ከዚህ ሁነት አኳያ በትክክልም የጂሚ ሆጋን አስተምህሮ ወራሾች ሆነዋል፡፡ ጂኦፍሪ ግሪን ስለ 1953ቱ የሃንጋሪ ገድል ሲያወሳ ቡድኑ በሌሎች የአውሮፓ ሃገራት በሚዘወተረው ረቀቅ ያለ የእግርኳስ አቀራረብ እና በብሪታኒያውያኑ ቀጥተኛ የአጨዋወት ዘይቤ መካከል እንደሚዋልል ጠቅሷል፤ አስተያየቱ ለእንግሊዞች ያደላና በከንቱ ውዳሴ የደለላቸው ቢያስመስልበትም ያነሳው ነጥብ ግን ሚዛን የሚደፋ ነበር፡፡ እንግሊዛውያኑ የሚደግፉት ረጅም-ቅብብሎች ላይ ያተኮረ ጨዋታ (Long-Ball Game) በዌምብሌዩ ታሪካዊ ፍልሚያ ሃንጋሪዎች በሁለትና ሶስት የመልሶ ማጥቃት ቅብብሎች (Counter Passes) ከመከላከል ወደ ማጥቃት ሲሸጋገሩ ዘዴያቸው የተሳካ እንደነበር ተረጋግጧል፡፡ ከዚህ አንጻር ጉትማን  ወደ ብራዚል ያመጣው የእግርኳስ መጨረሻ ግብን እንጂ 4-2-4 ፎርሜሽንን አልነበረም።

ብዙውን ጊዜ አጫጭር ድራማዊ ትዕይንቶችን በመጻፍ የሚታወቀው ብራዚላዊው ኔልሰን ሮድሪጌዝ የጨዋታ አቀራረብ ልዩነትን በተመለከተ ጥሩ ጥንቅር አቅርቧል፡፡ በጽሁፉ የእግርኳሱን ታዋቂ ሰዎች ገሃዳዊ-ዓለም የሚበረብሩ ምናባዊ ቃለ-ምልልሶችን አካቷል፡፡ ጋዜጠኛው የኻኖቭድን ወደ ብራዚል መድረስ አሰመልክቶ ፌሬንክ ፑሽካሽ እና ከሃገሪቱ የእግርኳስ ጀግኖች መካከል አንዱ የሆነው ዘዚንሆን ያሳተፈ፣ እያንዳንዳቸው በጨዋታ ወቅት የሚከውኑት እጅግ ምትሃታዊው ድርጊት የትኛው እንደሆነ የሚያስቃኝ ጥያቄዎችን አቅርቧል፡፡ ዚዚንሆ ለጓደኞቹ ግብ የሚሆኑ ኳሶችን ማመቻቸት እንደሆነ መለሰ፤ የፑሽካሽ ምላሽ ብዙ የሚያስገርም አልነበረም፤ ጎሎችን ማስቆጠር የእርሱ ተቀዳሚ ምርጫ መሆኑን አሳወቀ፡፡በእርግጥ ተምሳሌቱ የተጫዋቾቹን ድንገታዊ የሜዳ ላይ ፍላጎትና ቅጽበታዊ ውሳኔ የሚገልጽ ሊሆን ይችላል፤ ነገርግን ምሳሌው በወቅቱ  የብራዚላውያን እግርኳስ የተግባራዊ እውነታ (Pragmatism) ችግር እንደነበረበት ማሳያ ይሆናል።

በ1956 ሳኦፖሎ ዓመቱን ሙሉ ደካማ ብቃት አሳየ፤ በፓውሊስታ ሻምፒዮናም ከሊጉ አሸናፊ ሳንቶስ በሰባት ነጥቦች ተበልጦ ሁለተኛ ሆኖ ጨረሰ፡፡ ለቡድኑ 1957ም አልሆነለትም፤ አጀማመሩን በጥሩ ብቃት ማጀብ ተሳነው፤ የመጀመሪያውን የውድድር ዘመን ከመሪው ኮረንቲያንስ በሰባት ነጥቦች ርቆ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ አጋመሰ፡፡ ቀስ በቀስ ግን የጉትማን እግርኳስ አጨዋወት ዘዴዎች ፍሬያማ መሆን ጀመሩ፡፡  

ጉትማን በሳኦፖሎ የልምምድ ማዕከል የሚገኘው ሰፊ ግድግዳ  ላይ በተመሳሳይ ርቀት ቋሚና አግዳሚ መስመሮችን አስቀለመ፡፡ ወደ ላይ እና ወደ ጎን እኩል ልኬት ያላቸው በርካታ ጎነ አራት ስፋቶችን (Squares) የያዙ ምስሎች (Grids) ተፈጠሩ፡፡ የሥልጠናው መርኃግብር ሲጀምር ኳስ ለአጥቂዎች እየሰጠ ተጫዋቾቹ እርሱ የሚፈልገውን የካሬ ምስል እንዲመቱ ይጮኽባቸው ጀመር፡፡ ለመሃል አጥቂዎች (Centre-Forwards) የሚታለሙ ረጃጅም ቅብብሎች (Long Balls) አልፎአልፎ እንዳስፈላጊነታቸው ለመስመር አማካዮች (Wingers) እንዲጣሉ ያስገድድ ገባ፡፡ ተጫዋቾቹ ፈጣን ቅብብሎች (Rapid Passing) የሚከውኑባቸውን የልምምድ ዘዴዎች በማበጀት ኳስ እግር ሥር እያቆዩ ማባከን ፍጹም ተገቢ እንዳልሆነም ማስረዳቱን ቀጠለ፤ በዚህም ምክንያት “ጠቅ-ጠቅ-ጠቅ…” እና ” ተቀበል-ስጥ-አቀብል-ሒድ…” የተሰኙ ትዕዛዛት የአጫጭርና ፈጣን ቅብብሎች ሥልጠና ዘልማዳዊ አነጋገሮች ሆኑ፡፡ ሁሉም የተጫዋቾች እንቅስቃሴ ኳሷን በፍጥነት ወደ ፊት ከመግፋት ጋር የሚያያዝ እና ተጫዋቾቹ በደመነፍሳዊ ምሪት ሲጫወቱ ማየት የአሰልጣኙ ፍላጎት ነበር፡፡ ከሪዮ ከተማ የባንጉ ክለብ ተጫዋች የነበረውን የሰላሳ አራት ዓመቱን ዚዚንሆ ማስፈረሙ በጣም ጠቃሚው እርምጃ ሳይሆን አልቀረም፡፡ ጉትማን ከሁለቱ የመሃል አማካዮች ይበልጥ በፈጠራ ሥራ ላይ የሚያተኩረውን ሚና ለዚዚንሆ ሰጠው፤ ከዚያ ቀደም ከአጥቂዎች ጀርባ ሆኖ በጨዋታ አቀጣጣይነት (Playmaker) የተጫወተውን ዲኖ ሳኒ ደግሞ በጥልቀት ወደኋላ ተስቦ የመከላከል ኃላፊነት እንዲወጣ አደረገ፡፡ ይህ ውሳኔው በቤነፊካ ጉትማን ማሪዮ ኮሉናን በየትኛውም መንገድ እንደሚያጫውተው ቅድመ ማስጠንቀቂያ የሰጠና ፍንጭ ያሳየም ነበር፡፡ ለዚያም ይሆናል አሰልጣኙ “ይህን ለውጥ ሳደርግ ብቻ ነው መጫወት የጀመርኩ የሚመስለኝ፡፡” ያለው።

ጉትማን ከብራዚል ሹልክ ብሎ ወደ አውሮፓ በኮበለለበት ዓመት ሳኦፖሎ የሻምፒዮናው ባለድል ሆነ፡፡ ቪሴንቴ ፊዮላም የሃንጋሪያዊውን አሰልጣኝ በጎ ተጽዕኖ በክለቡ ሊያስቀጥል ቻለ፡፡ ፊዮላ አማካኝ የተጫዋችነት ብቃት ይዞ ሳኦፖሎ በ1949 የፓውሊስታ ሻምፒዮናን ድል እንዲጎናጸፍ የበኩሉን አስተዋፅኦ አበርክቷል፡፡ ጉትማንን በረዳት አሰልጣኝነት እያገለገለም በክለቡ ቆይቷል፡፡ ለ1958ቱ የዓለም ዋንጫ የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ ሲሾም ብዙዎች ተገርመዋል፡፡ በ1957ቱ የደቡብ አሜሪካ ዋንጫ ሃገሪቱ ሶስተኛ ደረጃ ይዛ ስታጠናቅቅና ኦዝቫልዶ ብራንዳኦ ከቡድኑ እንዲለቅ ሲገደድ ወዲያውኑ በተከታታይ እርሱን የተከቱት ሁለቱ አሰልጣኞች ሲልቪዮ ፒሪሎ እና ፔድሪንሆ በፊዮላ ሹመት አልተደነቁም፡፡ በእርግጥ ከዚያ በፊት ፍሌይታስ ሶሊችን የመቅጠር ጥረት ተደርጎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሶሊች ፓራጓዊ መሆኑ አላስወደደውም፡፡ ስለዚህም የብራዚል እግርኳስ ማህበር በፍጥነት ፊቱን ወደ ፊዮላ በማዞር አስተማማኝና አወዛጋቢ ያልሆነ ምርጫ አደረገ፡፡ ፊዮላ ምግብ በማብሰል ጥበብ የተካነ፣ በዚህም ሳቢያ እጅጉን የሚመገብና በጣም የተረጋጋ ሰው ነበር፡፡ የአሉባልታዎቹ ትክክለኝነት አጠራጣሪ ቢሆንም አሰልጣኙ በልምምድ ሰዓት በተቀያሪ ተጫዋቾች ወንበር ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች ሸለብ ይል እንደነበር ይወራበታል፡፡ የጋሪንቻን ግለ-ታሪክ የጻፈው ሩይ ካስትሮ የፊዮላ መጠን ያለፈ ውፍረት የልብ ደም ቧንቧ መኮማተር ችግር (Coronary Spasm) እንዳመጣበት ይናገራል፡፡ ” በሽታው ሲነሳበት ደረቱ አካባቢ የሚሰማው ከባድ ውጋት ክፉኛ ያሰቃየው ነበር፡፡ ስለዚህም ራሱን ከዚህ ድንገተኛ የህመም ስሜት ለመታደግ ሲል አይኖቹን ጨፍኖ አንገቱን ወደታች ዝቅ ያደርግና የደም ቧንቧዎቹ የመኮማተር ሒደት እስኪያልፍለት ይጠብቃል፡፡ ይህ መደበኛ የጭንቅ ክንውን የፊዮላ የእለት ተዕለት ተግባር ነበር፡፡ የአሰልጣኙን ውስጣዊ የጤና ችግር በውል ሳይረዱ በንዴት ሲጦፉ የከረሙ ጋዜጦች በፓፓራዚ ፎቶዎች በመታገዝ የሰውየውን የሰቀቀን ድርጊት እንቅልፍ አድርገው ቆጠሩበት፡፡” በማለት ብራዚላዊው አሰልጣኝ ላይ የሚቀርብበት ወቀሳ አግባብ እንዳልነበር ይተነትናል፡፡ 

ፊዮላ ለአጭር ጊዜ ቦካ ጁኒየርስን ሲያሰለጥን በክለቡ በመሃል-ተከላካይ አማካይነት (Centre-Half) የተጫወተው አርጀንቲናዊው አንቶኒዮ ራቲን ግን የሩይ ካስትሮን ሙግት የሚጻረር ሐሳብ ይሰጣል፡፡ ፊዮላ የልምምድ ጨዋታዎች ሲደረጉ አልፎ አልፎ እንደሚያንቀላፋ መከራከሪያ ገጠመኙን ያቀርባል፡፡ ” እያንዳንዱ የልምምድ መርኃግብራችን ሲገባደድ አንድ የእርስበርስ ግጥሚያ እናደርጋለን፤ ይህ የዘወትር ተግባራችን ነው፡፡ ከዕለታት በአንዱ እጅግ በጣም ሞቃት በሆነ ቀን ጨዋታችንን አደራነው፥ ማቆሚያ አልነበረንም- በጥሩ ስሜት ሆነን ፍልሚያችንን ቀጠልን፡፡ አሰልጣኛችን የዕረፍት ሰዓት መድረሱን የሚያሳውቀውን የፊሽካ ድምጽ እንዲያሰማን እየጠበቅን ነው- ነገርግን እርሱ ዝም ብሎ ተቀምጧል፡፡ እኛም የሆነ ነገር እንዲያደርግ ወደ እርሱ ማማተራችንን ተያያዝነው፤ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡ ስለዚህ ወደ እርሱ ተጠጋሁ፤ እያንኮራፋ አገኘሁት፤ እኛ ስንጫወት ፊዮላ ለጥ ብሎ ነበር፡፡” 

የፊዮላ የሰውነት ክብደትና ገራገር ባህርዩ የተለየ የእግርኳስ አጨዋወት ሥልት ከመተግበር ወደኋላ እንዲል አላስገደዱትም፤ ብራዚላዊው በጨዋታ ውበት የሚደሰት አሰልጣኝ ነበር፡፡ የሃገሪቱ እግርኳስ ማህበር ሰዎችም ቀድሞ እንደጠበቁት ሰውየው እንዲሁ በቀላሉ የሚፈነግሉት አይነት አልሆነላቸውም፡፡ የ1958ቱ የብራዚል ቡድን ከጁሴሊኖ ኩቢሼክ መንግስት በተገኘ ድጋፍ በሃገሪቱ እግርኳስ ታሪክ ምሉዕ እና ምርጥ ዝግጅት አድርጓል፡፡ ብሄራዊ ቡድኑ ወደ አለም ዋንጫ አዘጋጇ ሃገር ሲውዲን ከማቅናቱ በፊት የልዑካኑ መሪዎች ቀድመው በመሄድ ሃያ አምስት የተለያዩ የልምምድ ቦታዎችን ከጎበኙ በኋላ ለፊዮላ ቡድን ተስማሚ ያሉትን የመለማመጃ ሥፍራ ለመምረጥ ችለዋል፡፡ በሆቴሉ የሚሰሩ ሃያ አምስት እንስት ሰራተኞች የብዙዎችን ትኩረት ስበው በተጫዋቾች ዘንድ የብቃት መዋዠቅ እንዳይከሰት በወንዶች እንዲተኩ ተደርጓል፡፡ በሃገሪቱ (ሲውዲን) እርቃናቸውን የሚንቀሳቀሱ ሰዎች የሚሰባሰቡበት ማጎሪያ ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ ዝግ እንዲሆን ጠይቀውም ነበር-አዎንታዊ ምላሽ አላገኙም እንጂ፡፡ 

በወቅቱ የብራዚል ብሄራዊ ቡድን የህክምና ዶክተር፣ የጥርስ ሃኪም፣ የአካል ብቃት አሰልጣኝ፣ ገንዘብ ያዥ፣ የስነልቦና ባለሙያና የተጋጣሚ ቡድን እንቅስቃሴን እንዲሰልል ቀደም ሲል የፍሎሚኔንሴን ክለብ ያሰለጠነው ኤርኔስቶ ሳንቶስን አካቶ ነው ወደ አውሮፓ የተጓዘው፡፡ በተጫዋቾቹ የቅድመ-ጤና ምርመራ ውጤት መሰረት አብዛኞቹ በጥገኛ የአንጀት ተህዋስያን ስለተጠቁ ማርከሻ መድሃኒት እንዲጠቀሙ፣ አንደኛው ደግሞ ከአባላዘር በሽታዎች መካከል በቂጥኝ ስለተያዘ ህክምና እንዲከታተል አዘዘ፡፡ የቡድኑ ጥርሥ ሐኪም በጊዜያዊ የሃገሪቱ ስብስብ አባለት ውስጥ ሰላሳ ሶስት የሚደርሱትን ተጫዋቾች ጥርሥ በመንቀል ባተሌ ሆኖ ከረመ፡፡ ፊዮላ በእነዚህ ሁሉ እገዛዎችና ክትትሎች ደስተኛ ሆነ፤ ለስነልቦና ባለሙያው ዶ/ር ዣኦ ካርቫልሃስ ግን እምብዛም ትኩረት አልሰጠውም።

ከዚያ ቀደም አዘወትሮ የከተማ አውቶቡስ ሾፌር ለመሆን አመልካቾች የሚያስፈልጋቸውን ስነልቦናዊ  ዝግጅት የሚገመግመው ካርቫልሃስ ተከታታይ ፈተናዎችን ለቡድኑ ያቀርብ ነበር፡፡ ከሁሉ ከሁሉ ተጫዋቾቹ የወንድ ምስል እንዲስሉ ያስተላለፈው ትዕዛዝ እጅጉን የፌዝ መሰለበት፡፡ ስለዚህም የተሰጡት አብዛኞቹ  ምላሾች አስገራሚዎች ሆኑ፡፡ ተጫዋቾቹ በችኮላ በነጠላ ቋሚ  መስመር ላይ የጭንቅላት ምስልን ለመወከል ከላይ የክብ ምልክት እንዲሁም እጅና እግር የሚያመላክቱ ወደ ታች ያዘነበሉ አጫጭር መስመሮችን በቋሚ መስመሩ ላይ በመቀጠል ሰርተው አቀረቡ፤ ለተጫዋቾቹ ሙሉ የሰው ምስል ለማስመሰል የሚያስችሉ ጥቃቅን ዝርዝሮችን ከማሳየት ይልቅ በፍጥነት ቀላልና ወካይ ምናባዊ ምስል መፍጠር ተሻላቸው፡፡ካርቫልሃስም ይህን መልስ በአሉታዊ ጎን ተመለከተውና የተጫዋቾቹን ደመነፍሳዊ ውሳኔ መዘነበት፡፡ በመጨረሻ የስነልቦና ባለሙያው የደረሰበት ድምዳሜ እጅጉን የለበጣ ሆኖ ተገኘ፡፡ መጀመሪያ ” ፔሌ ገራገር ባህርይ ስለነበረው ለቡድን ሥራ አልያም ለህብረት ጨዋታ የሚያስፈልግ ኃላፊነትን የመሸከም አቅም አልያዘም፡፡” አለ፡፡ በስዕል ፈተናው መመዘኛ ጋሪንቻ ማግኘት ከሚጠበቅበት 123 ነጥብ 32ቱን ብቻ በማስመዝገቡ በሳኦፖሎ የከተማ አውቶቡስ ለማሽከርከር የሚያስችለውን ዝቅተኛ ውጤት ማምጣት አልሆነለትም፡፡ እናም ካርቫልሃስ ጋሪንቻ ከፍተኛ ጫና ላለባቸው ጨዋታዎች ብቁ እንዳልሆነ አስተያየቱን ሰጠ፡፡ ፊዮላ ግን የስነ ልቦና ባለሙያውን ሐሳቦች ከቁብ አልቆጠራቸውም፤ ይልቁንም ሁሉቱንም ጋሪንቻና ፔሌን የቡድኑ አባላት አደረጋቸው፡፡ 

በእርግጥ ሁለቱም ተጫዋቾች በውድድሩ መክፈቻ ለመጫወት አልቻሉም፡፡ እንደተጠበቀው ብራዚል ኦስትሪያን በቀላሉ 3-0 አሸነፈች፤ ፔሌ ጉዳት ገጥሞት አልተሰለፈም፤ ከኦስትሪያው ጨዋታ ቀደም ብላ ብራዚል ከፊዮረንቲና ጋር አቋሟን ለመፈተሽ ባደረገችው የወዳጅነት ግጥሚያ ጋሪንቻ የተጋጣሚ ቡድን ተጫዋችን ክብር በሚቀንስ መልኩ በረኛውን ካለፈው በኋላ ኳሷን በቀጥታ ወደ ግብ ከመስደድ ይልቅ ግብ ጠባቂው ተመልሶ እስኪመጣ ለመጠበቅ ወሰነ፤ በረኛው እንደምንም ብሎ አገግሞ ሲመጣ ጋሪንቻ እንደገና ቴክኒካዊ ክህሎቱን ተጠቅሞ አለፈውና ኳሷን ወደ መረቡ ላካት፡፡ በዚህ ድርጊቱ ከአሰልጣኙ ምርጫ ውጪ ሆነ፤ ለብዙዎች ፊዮላ ጋሪንቻን የሚያሰልፈው መስሎ ተሰማቸው፤ ነገርግን ያ አልሆነም፡፡ አሰልጣኙ የተጋጣሚ ቡድኖችን የሚገመግምለት ሳንቶስ በW-M ፎርሜሽን በአራት አማካዮች የተዋቀረው የኦስትሪያውያኑ መሃል ክፍል ያን ያሀህል እንደማያሰጋቸው ባይገልጽለት ኖሮ ጋሪንቻን ያሰልፈው ነበር፡፡ ፊዮላ በግራው መስመር ወደ ኋላ አፈግፍጎ መጫወት በሚችለው ማሪዮ ዛጋሎ ላይ ከፍተኛ እምነት ማሳደር ቢችልም ተጫዋቹ ግን የኦርሶሪዮን ሚና ለመወጣት ተገደደ፤ ይሁን እንጂ ሽግሽጉ ጋሪንቻን በተፈጥሯዊ ክህሎቱ የሚሰጠውን ግልጋሎት ማስገኘት አላስቻለም፡፡ ስለዚህም ዛጋሎ ጥብቅ የታክቲክ ሥርዓት አክባሪውንና የፍላሚንጎውን ጆኤል መምሰል ተጠበቀበት፡፡ 

እነዚህ ሁለት ተጫዋቾች (ፔሌና ጋሪንቻ) ከእንግሊዝ ጋር በሚደረገው ጨዋታም በድጋሚ ቋሚ ተሰላፊ ሳይሆኑ ቀሩ፡፡ ውሳኔው የብራዚል የአሰልጣኞች ቡድን ነበር፡፡ ይህም በመላው ዓለም በማደግ ላይ የነበረውን የፕሮፌሽናሊዝም ሥርዓት በተጫዋቾች ዘንድ የማስረጽ ሒደት ማሳያ ሆነ፡፡ የቶተንሃሙ አሰልጣኝ ቢል ኒኮልሰን የብራዚል ብሄራዊ ቡድንን እንዲገመግም ተላከ፤ እናም ብራዚሎችን ለማቆም ዲዲ የተባለውን ተጫዋች በቁጥጥር ሥር ማድረግ የግድ እንደሆነ አሳወቀ፡፡ የእንግሊዙ አሰልጣኝ ዋልተር ዊንተርቦተም በኒኮልሰን ሃሳብ ላይ ተመርኩዘው የብራዚሎችን የማጥቃት ሒደት ለመከላከል የሚያስችል አዲስ የታክቲክ ስልት ነደፉ፡፡ ይሁን እንጂ ታክቲካዊ ለውጡ ቀድሞ የተሰራበትና ተጫዋቾቹ የተዋሃዱት አልነበረም፡፡ በዌስትብሮሚች አልብዮን ክለብ በመሥመር ተከላካይነት የሚጫወተው ቁመተ መለሎው ዶን ሃው ከቢሊ ራይት ጎን በተደራቢ የመሃል- ተከላካይ አማካይነት (Second Centre-Half) እንዲሰለፍ ተወሰነ፡፡ በዎልቭስ በመሃለኛው የሜዳ ክፍል በቀኝ መስመር አማካኝነት የሚሰለፈው ኤዲ ካምፕ ከቶማስ ባንክስ ጋር ተጣምረው የሚያጠቁ የመሥመር ተከላካዮች (Attacking-Fullbacks) በመሆን ለአማካይ ክፍሉ ድጋፍ እንዲሰጡ ታሰበ፡፡ ቢል ስላተር ደግሞ ብራዚላዊውን ዲዲ የገባበት እየገባ በቅርብ ርቀት እንዲከታተለው ታዘዘ፡፡ በጨዋታው ላይ የብራዚሉ ቫቫ ጥሩ ሙከራ አድርጎ የግብ አግዳሚ መለሰበት፡፡ ብራዚሎች እንግሊዞቹ ላይ ተደጋጋሚ የማጥቃት ሒደቶችን ፈጸሙ፤ ተከላካዩ ክላምፕ አንደኛዋን ለጎልነት የቀረበች ኳስ ከመስመሩ ላይ እንደምንም ብሎ አወጣት፤ የእንግሊዛውያኑ ግብ ጠባቂ ኮሊን ማክዶናልድ ሁለት አደገኛ ሙከራዎችን አምክኖ ብሄራዊ ቡድኑን ታደገ፡፡ ጆዜ አልታፊኒ በግንባር የገጫቸው ግብ ሊሆኑ ጥቂት የቀራቸውን ኳሶች በረኛው በአስገራሚ ብቃት መለሳቸው፡፡ ብራዚላዊው አልታፊኒ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በጣልያናዊው ሳንድሮ ማዞላ ቅጽል ስም የሚጠራ ጎል አነፍናፊ አጥቂ ነበር፡፡ የዊንተርቦተም የመከላከል ታክቲክ ብራዚላውያኑን ተጫዋቾች እንዳሻቸው እንዳይነቀሳቀሱ አደረጋቸው፤ አጥቂዎቹም ግብ ከማስቆጠር ታቅበው ዋሉ፤ እንግሊዝ ከብራዚል ያለ ጎል አቻ ተለያየች፡፡

ውጤቱ ብራዚልን በምድቧ ከሶቭየት ህብረት ጋር በምታደርገው የመጨረሻ ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ከተታት፡፡ የሃገሪቱ ብሄራዊ ቡድን ይህን ካላደረገ ወደ መጨረሻዎቹ ስምንት ቡድኖች አያልፍም፡፡ የቡድኑ ሥነልቦና ባለሙያ ካርቫልሃስ ተጨማሪ ፈተናዎችን ለተጫዋቾቹ መስጠት ጀመረ፡፡ ፈተናው ወደ ተጫዋቾቹ አዕምሮ ቀድሞ የሚመጣውን ማንኛውንም ነገር እንዲስሉ የሚጠይቅ ነበር፡፡ ጋሪንቻ ክብ ስዕል ሳለና በዙሪያው የጨረሮችን ምልክት አስቀመጠ፤  እንደነገሩ የተሳለ የጸሃይ ምስል ይመስል ነበር፡፡ ካርቫልሃስ ምስሉ ምንን እንደሚያመለክት ጋሪንቻን ጠየቀው፡፡ የተጨዋቹ ምላሽ የቧልት ይዘት ሳይኖረው አልቀረም፤ በቦታፎጎ የቡድን ጓደኛው የሆነው ኳረንቲንሃን ጭንቅላት እንደሚመስል ገለጸለት፡፡ ካርቫልሃስ ወዲያውኑ ጋሪንቻን ከምርጫው ውጪ አደረገው፤ በአጠቃላይ ፈተናውን ከወሰዱ ተጫዋቾች ውስጥ ዘጠኙ ለእንዲህ አይነቱ ከባድ ጫና ያለበት ጨዋታ ፍጹም ብቁ እንዳልሆኑ ለፊዮላ አሳወቀ፡፡ እንደ እድል ሆኖ አሰልጣኙ በራሱ ብያኔ እምነት አሳደረ፤ ሁለቱንም ተጫዋቾች ፔሌና ጋሪንቻን በቋሚነት ለማሰለፍ ወሰነ፡፡ ፔሌ ሁኔታውን ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፥ ካርቫልሃስን እንዲህ ስል ተናገርኩት፡- “….. ልክ ልትሆን ትችላለህ፤ ነገርግን አንተ ስለ እግርኳስ ምንም የምታውቀው ነገር የለም፡፡”

ከሶቭየቱ ጨዋታ በፊት ፊዮላ ስለ ሩሲያውያኑ የላቀ የተጫዋቾች የአካል ብቃት ደረጃ በሚወጡ ዘገቦች ሥጋት ገባው፡፡ ስለዚህ ጨዋታው ከሚከናወንበት ቀን ቀደም ብሎ ተጫዋቾቹ የብራዚላውያንን ተፈጥሮአዊ የእግርኳስ ተሰጥኦ በማሳየት ተጋጣሚዎቻቸው የሚርዱበትን መንገድ እንዲፈጥሩ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ጨዋታው ሊጀመር ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ ዲዲ ከመልበሻ ክፍሉ ከመውጣቱ በፊት ይህን አለው፡፡ ” አስታውስ! የመጀመሪያውን ኳስ ለጋሪንቻ ስጠው፡፡”  

ጨዋታው ተጀምሮ ኳሷ የብራዚሉ የመሥመር አማካይ ጋር እስክትደርስ ድረስ ሃያ ሰከንዶች ብቻ ፈጀባት፡፡ ብራዚላዊው ምትሃተኛ እግር ሥር ኳስ ስትደርስ ሰፊ ልምድ ያለው የሶቭየቱ የግራ መስመር ተከላካይ ቦሪስ ኩዝኔሶቭ ጋሪንቻን ቀረበው፡፡ ጋሪንቻም በአስደናቂ ሁኔታ በአብዶ ወደ ግራ አስመስሎ ወደ ቀኝ ሄደበት፤ ተከላካዩ በአካባቢው ብቻውን ቀረ፤ ተመልሶ እስኪመጣ ጋሪንቻ  ኳሷን ይዞ ጠበቀው፤ ኩዝኔሶቭ መጣ፤ በድጋሚ አለፈው፡፡ በተደጋጋሚ ሜዳ ላይ እስኪወድቅ ድረስ አብዶዎችን አከታተለበት፡፡ ጋሪንቻ ወደፊት ገፋ፤ ሌላኛውን ተጫዋች ዩሪ ቮይኖቭን በአስገራሚ ቴክኒክ ፊንታ ሰርቶ ከጀርባው ተገኘ፡፡ ወደ ሶቭየቶቹ የግብ ክልል ያለማንም ከልካይነት ያን ተዓምረኛ ተሰጥኦ እያሳየ ደረሰ፤ ከጠባብ ማዕዘን ጠንካራ ኳስ ወደ ግቡ መታ፤ ኳሷ የግቡን ቋሚ ታካ ወጣች፡፡ በደቂቃዎች ልዩነት ፔሌም የጎሉ አግዳሚ መለሰበት፡፡ ጨዋታው ጥቂት እንደሄደ ዲዲ የላከለትን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ (Through-Ball) ቫቫ ወደ ግብነት ቀይሮ ሃገሩን መሪ አደረገ፡፡ ጋብሬል ሃኖት እነዚያን ቅጽበቶች “በእግርኳሱ ዓለም የታዩ ከባዶቹ ሶስት ደቂቃዎች” ሲል ሰይሟቸዋል።

ብራዚል ተጋጣሚዋን 2-0 ድል አደረገች፤ ውጤቱ ጠባብ ቢመስልም ከስምንት ዓመታት በፊት የብሄራዊ ቡድኑ አባላት ስፔንና ሲውዲንን ሲያሸንፉ ያሳዩትን ልዩ ብቃት መድገም ቻሉ፡፡ በሩብ ፍጻሜው ዌልስ ያልተጠበቀና ጠንካራ አቋም አሳይታ ለብራዚል ፈተና ሆነች፤ በጉዳት ሳቢያ ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ ልጇን ጆን ቻርለስን ሳትይዝ በደቡብ አሜሪካዊቷ የእግርኳስ ኃያል 1-0 ብቻ ተረታች፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የብራዚል ቡድን ለተጋጣሚ የሚቀመሥ አልነበረም፡፡ በቁርጥ ቀን ልጇ ቦብ ያንኬ ጉዳት የተደናገጠችው ፈረንሳይ ብራዚልን በግማሽ ፍጻሜ የመግጠም እድል ደረሳት፤ በጨዋታው ፈረንሳውያኑ 5-2 ተደቆሱ፤ በፍጻሜው ሲውዲንም በተመሳሳይ ውጤት በብራዚል ተረታች፡፡ ብሪያን ግላንቪል ለብራዚል ብቃት መወድሱን አዥጎደጎደ፤ እንዲህም አለ፡፡ ” በአሁኑ ሰዓት ማንም በብራዚል ብቃት ጥርጣሬ ሊገባው አይቻለውም፤ በማራኪ አጨዋወቱ ተወዳዳሪ የሌለው ምርጡ ቡድን የዓለም ዋንጫውን አሸንፏል፡፡” 

በወቅቱ የጋሪንቻን ተፈጥሮዓዊ ችሎታ ለመጠቀም ሲባል የሚፈጠረውን ታክቲካዊ ክፍተት የማሪዮ ዛጋሎ ሚና ሚዛናዊ ያደርገው እንደነበር ፊዮላ ተናግሯል፡፡ ይህ የዛጋሎ የሜዳ ላይ ኃላፊነት እጅጉን ቁልፍ ጉዳይ ነበር፡፡ ቀደም ሲል ከመሃል አጥቂ ጎን የሚጫወት የፊት መስመር ተሰላፊ (Inside-Forward) የነበረው ዛጋሎ በብሄራዊ ቡድኑ ለመመረጥ ብቸኛው መንገድ ራሱን በመስመር አማካይነት ብቁ አድርጎ መገኘት እንደሆነ አመነ፡፡ ስለዚህም እንደፈለገ ወደኋላ እና ወደፊት እየተመላለሰ ለመጫወት ራሱን አዘጋጀ፡፡ በ1962ቱ የዓለም ዋንጫ ዛጋሎ ወደኋላ በጥልቀት አፈግፍጎ መጫወት ጀመረ፤ በዚህም ምክንያት የተጫዋቾቹ እንቅስቃሴያዊ የሜዳ ላይ አደራደር 4-3-3 ሆነ፡፡ የፊዮላ ህመም እያገረሸበት ሲያስቸግረው የተካውና ለቀጣዩ የዓለም ዋንጫ ተመሳሳይ የተጫዋቾች ስብስብ የመረጠው አይሞሬ ሞሬይራ ” በቺሊ ቆይታችን የተጫዋቾቻችን እድሜ ጉዳይ እጅጉን ያሳስበን ነበር፡፡ ከሌሎች ሃገራት አንጻር ታክቲካችን ተለዋዋጭ ያልሆነውም በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ቡድናችን ቀደም ሲል በሲውዲን ያሳየውን አብረቅራቂ ገድል እኛም እንድንፈጽም ተጠበቀብን፡፡ እያንዳንዱ ተጫዋች ለቡድኑ ሊሰጥ ከሚችለው ጥቅም አንጻር ነበር እንዲሰለፍ የምናደርገው፡፡ ለምሳሌ፦ ዲዲ ይበልጡን መሃል ሜዳ ላይ መንቀሳቀስ ያዘወትራል፤ የተጋጣሚ የማጥቃት ሒደትም እዚያው እንዲቋረጥ ይተጋል፡፡ 

ፈጣኑና በተደጋጋሚ የቦታ ለውጥ የሚከውነው ዚቶ ደግሞ በሜዳው ቁመት ወደኋላ እና ወደፊት እየተመላለሰ መከላከልና ማጥቃቱ ላይ ይሳተፋል፤ ተጫዋቹ ለሙሉ ዘጠና ደቂቃ ይህን ከማድረግ አይቦዝንም፡፡ በጥንቃቄ አንደኛው ተጫዋች ከሌላኛው ተጫዋች ጋር የሚኖራቸውን ወሳኝ መስተጋብር ለመፍጠር እንዲቻል የማጥቃት ሒደቱ መጠነኛ የስልነት ክፍተት ተፈጠረበት፤ ጥቂት ዘገምተኝነትም አሳየ፡፡ እንዲያም ሆኖ እያንዳንዱ ተጫዋች ልዩነት ማምጣት ከፈለገ የራሱን ፈጠራ ለመተግበር የሚችልበት ነጻነት ተሰጥቶታል፤ ይህም የድክመታችን ማካካሻ ሆኖልናል፡፡” በማለት የቡድኑን የተናጠል የተጫዋቾች ሚና በሰፊው ያብራራል፡፡ 

ይህንን ችግር በትልቁ የሚያካክሰው ጋሪንቻ ነበር ተጋጣሚዎች እርሱን ለመቆጣጠር በመደበኛነት ሁለትና ሶስት ተጫዋቾች ጥብቅ ክትትል እንዲያደርጉበት አዘዙ፤ ጋሪንቻ ግን በቀላሉ ያልፋቸው ገባ፡፡ በቺሊ ፔሌ በጉዳት ሳቢያ ከቡድኑ ከመራቁ በፊት የመጀመሪያዎቹን ሁለት የመክፈቻ ጨዋታዎች ብቻ አደረገ፤ ነገርግን ያን ያህል ልዩነት አልተፈጠረም፤ ለቀሪዎቹ ጨዋታዎች ጋሪንቻ ከበቂ በላይ ነበር፡፡ በሩብ ፍጻሜው ፍልሚያ እንግሊዝ ላይ የፍጹም ቅጣት ምት ቢያመክንም ሁለት ግቦች አስቆጥሮ ብራዚል የ3-1 ድል እንድትጎናጸፍ ትልቁን ሚና ተጫወተ፡፡ በግማሽ ፍጻሜው ደግሞ ቺሊ ላይ በተመሳሳይ ተጨማሪ ሁለት ጎሎች አግብቶ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጣ፤ ብራዚል ግን አዘጋጇን ሃገር 4-2 ከማሸነፍ ያገዳት አልነበረም፡፡ ጋሪንቻ ቅጣቱ ተነስቶለት ለፍጻሜው ጨዋታ ቢሰለፍም የተለመደ ብቃቱን ማሳየት አልሆነለትም፡፡ ምንም ማለት አልነበረም-ምክንያቱም የ1962 አጠቃላይ ውድድር የእርሱ ተጽዕኖ ያረፈበት ነበርና፡፡ በ1960ዎቹ አጋማሽ የመገለል በደል ሳይደርስበት ያሳካው የመጨረሻው ስኬቱ ይኸው የቺሊው የአለም ዋንጫ ድል ሆነ፡፡

በ1949 <ኤ-ጋዜታ> በተሰኘው ጋዜጣ ላይ ማዞኒ ይህን የንጽጽር ጽሁፍ አቀረበ፡፡ ” ለአንድ እንግሊዛዊ እግርኳስ የአካል ብቃትና የፍጥነት ልምምድ ጉዳይ ነው፤ ለአንድ ብራዚላዊ ግን መደበኛ ጨዋታ ነው፡፡ አንድ ተጫዋች ለሶስት ተከታታይ ጊዜያት ኳስን <ድሪብል> ሲያደርግ ማየት በአንድ እንግሊዛዊ ድርጊቱ እንደ አናዳጅ ተግባር ይቆጠርበታል፤ አንድ ብራዚላዊ ግን ይህን ክንውን እንደ ትልቅ ችሎታ ያየዋል፡፡ በእንግሊዝ እግርኳስ <ጥሩ ጨዋታ> የሚባለው በበርካታ ባለሙያዎች እንደሚቀመር የሙዚቃ ዝግጅት (Symphonic Orchestra) አይነት ሲሆን ነው፡፡ የብራዚላውያን እግርኳስ <ጥሩ ጨዋታ> ደግሞ እጅግ በጣም ደማቅ ድባብ በሚፈጥር የጃዝ ባንድ ይመሰላል፡፡ በእንግሊዝ ኳሷ ከተጫዋቹ እንድትፈጥን ይጠበቃል፤ በብራዚላውያኑ እግርኳስ ደግሞ ተጫዋቹ ከኳሷ መቅደም ይኖርበታል፡፡ እንግሊዛዊ ተጫዋች እንዲያስብ ይገደዳል፤ ብራዚላዊ ተጫዋች ግን እንዲፈጥር ነጻነት ይሰጠዋል፡፡” ይላል የንጽጽሩ ወግ፡፡ ታዲያ እነዚህን ልዩነቶች ከጋሪንቻ በላይ ሊያመላክት የሚችል ማንም አልነበረም፡፡ በሳኦፖሎ ክለብ ቤላ ጉትማን ካንሆቴይሮ የተባለ የግራ መስመር አማካይ (Left-Winger) ነበረው፡፡ ተጫዋቹ “ግራኙ ጋሪንቻ” (Left-footed Garincha) እየተባለ ይጠራ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ የአሰልጣኙን ትዕዛዝ በዘዴ ቸል ብሎ በአስገራሚ ሁኔታ በራሱ (በተጫዋቹ) መንገድ ካንሆቴይሮ እንዳሻው ሲሆን የተመለከተው ጉትማን ” ታክቲክ ለሁሉም ተጫዋቾች ይሰራል፤ ለካንሆቴይሮ ግን አስፈላጊ አይደለም፡፡” ሲል ተናገረ፡፡ እነዚህን በመሳሰሉት ተጫዋቾች ላይ ቀድሞ ባይተነበይም ቪክቶር ማስሎቭ እና አልፍ ራምሴይ እንዳረጋገጡት በአራት የኋላ መስመር ተከላካዮች የመጫወት ጥቅም  እንቅስቃሴያቸው በታክቲክ የማይገደብ ባለ ተሰጥኦ ተጫዋቾች ይበልጥ እንዲጎመሩ ማስቻሉ ነው፡፡ በእርግጥ የእግርኳሱ ዓለምም ይህ መልዕክት በአግባቡ ደርሶታል፡፡ በ1966ቱ የዓለም ዋንጫ ወቅት W-M ፎርሜሽን ያለፈበትና የቀደመ ታሪክ መሆን የጀመረው ከዚሁ በመነጨ እሳቤ ነውና፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሁለት ዓመታትም ዘጠኝ መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡