የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለሴካፋው ውድድር ዝግጅቱን ቀጥሏል

በዩጋንዳ አስተናጋጅነት የፊታችን ዕሁድ በካምፓላ በሚጀመረው የሴካፋ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ ተካፋይ የሆነው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በአዳማ ከተማ ዝግጅቱን በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

አስራ አንድ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በሚሳተፉበት በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በምድብ ሁለት ከኬንያ፣ ዛንዚባር እና ታንዛኒያ ጋር ከቀናት በፊት በወጣው ዕጣ መሠረት የተደለደለች ሲሆን ቡድኑም ለዚህ ውድድር ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ ከነሐሴ 27 ጀምሮ በአዳማ ራስ ሆቴል በመክተም ዝግጅታቸውን በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ላይ እያደረጉ ይገኛሉ። ቡድኑ በስፋት ያለፉትን ቀናት በልምምዱ ላይ ትኩረት ያደረገው ከጠንካራ የሜዳ ላይ ስራዎች ባለፈ በተጫዋቾቹ ስነ ልቦና ላይም እንደሆነ አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

አስቀድሞ ብሔራዊ ቡድኑ 28 ያህል ተጫዋቾችን በመምረጥ ወደ ዝግጅት የገቡ ሲሆን ሀብታሙ መኮንን (አጥቂ ከሀዋሳ ከተማ)፣ አዛርያስ አቤል (ተከላካይ ወላይታ ድቻ)፣ ሀብታሙ ኃይሌ (ተከላካይ መከላከያ) እና አቡሽ አበበ (ግብ ጠባቂ ወላይታ ድቻ) ኋላ ላይ ቡድኑን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ በቅድሚያ ከተቀነሱ ተጫዋቾች በተጨማሪም ሰኞ ዕለት ከቡድኑ ጋር ሲሰሩ የቆዩ አራት ተጫዋቾች ተቀንሰው በድምሩ 21 ተጫዋቾች ቀርተዋል። የተቀነሱበት ምክንያት ደግሞ ከአንድ ዓመት በፊት በተዘጋጀው የሴካፋ ከ17 ዓመት በታች ውድድር ላይ ብሔራዊ ቡድናችን ውስጥ ተካተው ሲጫወቱ በወቅቱ ዕድሜያቸው 15 ያልሞላቸው በመሆኑ እና አሁንም የፓስፖርት ዕድሜያቸው 17 ያልሞላቸው እንደሆነ በመመላከቱ ምክንያት ነው ተብሏል። የተቀነሱት ተጫዋቾችም በየነ ባንጃው፣ ወንድማገኝ ኃይሉ፣ ኢያሱ ለገሰ እና ዳዊት ባህሩ ናቸው፡፡

ቡድኑ ችግሮችን በመቋቋም ጭምር እየተዘጋጀ መሆኑን ሶከር ኢትዮጵያ በስፍራው ተገኝታ ከመመልከቷ ባለፈ የቡድኑ አባላት ቅሬታቸውን ገልፀዋል፡፡ የቅርብ ክትትል እየተደረገለት የማይገኘው እና ዘጠኝ ቀናትን ልምምድ ከጀመረ ያስቆጠረው ይህ ብሔራዊ ቡድን ከትጥቅ አቅርቦት ጋር በተገናኘ ተጫዋቾቹ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ በተለይ የመመገቢያ ትጥቅ ባለመኖሩ በራሳቸው የግል ልብስ እየተጠቀሙ የሚገኝ ሲሆን በልምምድ ወቅትም ፌዴሬሽኑ ማቅረብ የነበረበት ጫማ እና መሰል ቁሳቁሶች ሳይሰጥ በመቅረቱ ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልፀዋል።

ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቡድኑ አባላት መቼ ወደ ዩጋንዳ እንደሚያመሩ ባይገፅም ባገኘነው መረጃ መሠረት 20 ተጫዋቾችን በመያዝ ቅዳሜ ወደ ስፍራው እንደሚጓዙ ሲጠበቅ ከዋናው ብሔራዊ ቡድን ጋር መቐለ የሚገኘው አጥቂው መስፍን ታፈሰ በመቐለ ከሚደረገው የሩዋንዳ የቻን ማጣሪያ ጨዋታ በኃላ ዘግይቶ ቡድኑን የሚቀላቀል ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ