ሲዳማ ቡና ሁለት ተጫዋቾችን አስፈረመ

ሲዳማ ቡና በዛሬው ዕለት የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር በመፈፀም የአዳዲስ ተጫዋቾቹን ብዛት አምስት ሲያደርስ ፀጋአብ ዮሴፍ እና እሱባለው ሙሉጌታ በክለቡ ስብስብ ውስጥ የተካተቱ አዲስ ፈራሚዎች ሆነዋል።

ከሀዋሳ ከተማ የታዳጊ ቡድን የተገኘው ፀጋአብ ዮሴፍ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከታዩ ጥሩ የአማካይ ስፍራ ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡ በሀዋሳ ከተማ የ17 እና 20 ዓመት በታች ቡድኖች ከተጫወተ በኃላ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሀዋሳ ቆይታ ወቅት ወደ ዋናው ቡድንም አድጎ ተጫውቷል፡፡ አማካዩ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በፋሲል ከነማ አሳልፎ ቀሪ የውል ጊዜ እያለው ወደ ትውልድ ከተማው ሀዋሳ በመመለስ ማረፊያውን ሲዳማ ቡና አድርጓል፡፡

ሌላኛው ለሲዳማ ቡና ለመጫወት የተስማማው የመስመር አጥቂው እሱባለው ሙሉጌታ በአዲስ አበባ ከተማ የተስፋ ቡድን ጅማሮውን አድርጎ በ2008 ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ሲጫወት የቆየ ሲሆን አሁን ደግሞ የአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ቡድንን መቀላቀሉ ታውቋል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ