ሴካፋ ከ20 ዓመት በታች| ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያለፉ ቡድኖች ተለይተዋል

የሴካፋ ዋንጫ ዛሬም በጎል በተንበሸበሹ ጨዋታዎች ቀጥሎ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ያለፉ ሀገራት ሲታወቁ ኢትዮጵያውያን ዳኞችም ሁለት ጨዋታዎችን መርተዋል።

በጉሉ እና ንጂሩ ስታድየሞች የተካሄዱት የዛሬ ጨዋታዎች እንደ ባለፉት ጨዋታዎች ሁሉ በርካታ ግቦች ሲቆጠሩበት ኤርትራ፣ ታንዛንያ፣ ሱዳን እና ኬንያ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አልፈዋል።

ኢትዮጵያዊው ለሚ ንጉሴ የመራው የዩጋንዳ እና የታንዛንያ ጨዋታ ሳይጠበቅ በታንዛንያ 4-2 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ ሌላው በጉሉ ስታዲየም በሱዳን እና ደቡብ ሱዳን መካከል የተካሄደው ጨዋታም በሱዳን 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በንጅሩ በ8:00 የተካሄደው እና ኢትዮጵያዊው የመሃል ዳኛ በላይ ታደሰ የመራው የኬንያ እና ብሩንዲ ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ተደርጎበት ኬንያ በቤንሶን ኦሎች የተጨማሪ ሰዓት ግብ ታግዛ 2-1 አሸንፋለች። በዚሁ ሜዳ የተካሄደው ሁለተኛው ጨዋታ የዛንዚባር እና የኤርትራ ጨዋታ ሲሆን ኤርትራ 5-0 አሸንፋለች።

አዘጋደጇ ዩጋንዳ ጨምሮ ደቡብ ሱዳን፣ ብሩንዲ እና ዛንዚባርን የሸኘው ውድድሩ በቀጣይ በግማሽ ፍፃሜው ኤርትራን ከ ኬንያ፤ ሱዳንን ከ ታንዛንያ ያገናኛል።


© ሶከር ኢትዮጵያ