የቀድሞ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ቶም ሴንትፌት ስማቸው ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ብድን አሰልጣኝነት ስራ ጋር ተያይዞ መነሳቱ የተሳሳተ መረጃ እንደሆነ ዛሬ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡
የቶጎ ብሄራዊ ቡድን እያሰለጠኑ የሚገኙት አሰልጣኙ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ስራ ገበታቸው ላይ እንዳሉ እንደሚያውቁም ጨምረው ተናግረዋል፡፡ “በመጀመሪያ የስራ ቅጥር ይውጣ አይውጣ የማውቀው ነገር የለም፡፡ ባለኝ መረጃ መሰረት ዮሃንስ በስራ ገበታው ላይ ይገኛል፡፡ አሰልጣኙን አከብራለው፡፡ ስለዚህ በሌለ ስራ ላይ ማውራት አግባብ አይደለም፡፡
” ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮጵያ የሚገኙ እግርኳስ ወዳድ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ እንድመለስ ጥያቄ አቅርበውልኛል፡፡ አውነት ነው ኢትዮጵያን እና እግርኳሷን እወዳለው፡፡ ሁለት ግዜ ወደ ዋሊያዎቹ የመመለስ ዕድል ነበረኝ፡፡ ነገር ግን ፌድሬሽኑ ሌላ አሰልጣኝ በመሾሙ ሳይሳካ ቀርቷል::” ብለዋል፡፡
የ42 ዓመቱ ሴንትፌት አክለው የቶጎ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ መሆናቸውን ብቻ እንደሚያወቁ ተናግረዋል:: “ወደፊት ኢትዮጵያን እንደማሰለጥን ተስፋ አለኝ፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት የቶጎ አሰልጣኝ መሆኔን ብቻ ነው ማውቀው፡፡ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ምድባችንን ከቱኒዚያ እና ላይቤሪያ ቀድመን እየመራን ነው፡፡ ስለሌላ ስራ የማስብበት ግዜ ላይ አይደለሁም፡፡ ዕቅዴ ቶጎን ለ2017 የአፍሪካ ዋንጫ ማሳለፍ ነው፡፡ ሌላ የሚወሩ ወሬዎች በመሉ ሀሰት ናቸው” ሲሉ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡