አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ በኬንያ ሊግ የማሰልጠን ፍላጎት እንዳላቸው ገለፁ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ ወደፊት የኬንያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦችን የማሰልጠን ዕድል ካጋጠማቸው በደስታ እንደሚቀበሉት ተናግረዋል። አሠልጣኙ ከሶካ ድረገፅ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኬንያ ሊግ በፍጥነት እያደገ እንደሚገኝ ጠቅሰው በሊጉ በአሠልጣኝነት ሰርተው ቢያልፉ ደስተኛ እንደሚሆኑ ነው የገለፁት።

የኬንያ ፕሪምየር ሊግን 10 ጊዜ ማንሳት የቻለው ተስከር ክለብ ከቀድሞ አሠልጣኙ ፍራንሲስ ኪማንዚ ጋር ከተለያየ በኋላ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ በኬንያ ጥቂት አመታት ያሳለፉትን አሠልጣኝ ዮሐንስ ለመቅጠር ንግግር ጀምሮ እንደነበር በስፋት የተነገረ ቢሆንም አሠልጣኙ ግን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

“የኬንያ ሊግ በቅርብ ጊዜያት ፈጣን ዕድገት በማሳየት በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ካሉ ጥሩ የሚባሉ የእግርኳስ ውድድሮች ውስጥ አንዱ መሆን ችሏል። በኬንያ ባሳለፍኳቸው ዓመታት ሃገሪቱንና ህዝቦቿን ወድጃቸው ነበር። ወደፊት ዕድሉን ካገኘሁም ያለጥርጥር ወደ ኬንያ ተመልሼ መስራት እፈልጋለሁ። በአሁኑ ጊዜ ግን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስራ ላይ ነው ሙሉ ትኩረቴን ያደረግኩት።”

አሠልጣኝ ዮሐንስ ቡድናቸው ከ2016ቱ የቻን ውድድር ውጪ ከሆነ በኋላ ሙሉ ትኩረታቸውን በመጋቢት ወር ወደሚቀጥለው የ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እንዳዞሩ አያይዘው ገልፀዋል።

“ሁለት ጨዋታ አድርገን በአንዱ አቻ ስንወጣ አንዱን ደግሞ ማሸነፍ ችለናል። ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ሰፊ ዕድል እንዳለን አምናለሁ። በሩዋንዳው ከተሳተፈው ቡድን ላይ የተወሰኑ ተጫዋቾችን ጨምረን ከቻን ውድድር ያገኘነውን ልምድ በመጠቀም ለጨዋታዎቹ እንቀርባለን።”

የ2017ቱ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በመጋቢት ወር ሲቀጥል ኢትዮጵያ ከአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የደርሶ መልስ ጨዋታ የምታደርግ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *