መረጃዎች | የ33ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

መረጃዎች | የ33ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች

33ኛው ሳምንት የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በሁለተኛ ቀን ዛሬ ቀጥሎ በሚደረጉ አራት ጨዋታዎች ይቀጥላል፤ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።

ሸገር ከተማ ከመቐለ 70 እንደርታ

በአርባ ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀመጡት ሸገሮች ያላቸው የነጥብ ልዩነት አስተማማኝ ባለመሆኑ አሸንፈው ከስጋት ቀጠናው ለመራቅ መቐለ 70 እንደርታን ይገጥማሉ።

ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ማግኘት ካለባቸው አስራ ስምንት ነጥብ ግማሹን አሳክተው ሁለት ጨዋታ አሸንፈው በሦስቱ ነጥብ በመጋራት በጥሩ መነቃቃት የነበሩት ሸገሮች በመጨረሻ ጨዋታ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት ማስተናገዳቸው የሚታወስ ሲሆን በተለይም የሊጉን መሪ በ31ኛው ሳምንት የማሸነፋቸው ምክንያት የሆነው የመከላከል ሁኔታ የቡድኑ እንደ ጠንካራ ጎኑ ይነሳል። ምንም እንኳን ከወራጅ ቀጠናው በስድስት ነጥብ ርቀው የሚገኙ ቢሆንም ከፍ ብለው ቀሪዎችን ጨዋታዎች በነፃነት ለመጨረስ የዛሬውን ውጤት አጥብቀው ይፈለጉታል። በተለይም ተጋጣሚው ወራጅ ቀጠና ላይ እየዳከረ ያለ ቡድን ከመሆኑ አኳያ ጨዋታው ከባድ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ግን ቡድኑ ግብ በማስቆጠር ላይ ያለው ጥንካሬ ላይ ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ውጤት ለማስጠበቅ መከላከሉ ላይ የሚያተኮር በመሆኑ ጨዋታውን አሸንፈው ከሽንፈት ያገግማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሠላሳ አንድ ነጥብ በመሰብሰብ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ የሚገኙት ምዓም አናብስት ካሉበት ስጋት ለመውጣት ዛሬ ወሳኝ ጨዋታ ያደርጋሉ።

ሀዋሳ ላይ ሁለት ተከታታይ ድሎችን አግኝተው በጥሩ ተነሳሽነት ቆይታቸውን ካገባደዱ በኋላ ላለፉት አራት ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ከብዷቸዋል። ፋሲል ከነማን 3ለ0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ ከተጋራ በኋላ ሁለት ተከታታይ ሸንፈት ያስተናገደው ቡድኑ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት ተከታታይ ድሎችን ካሳካው መድን ጋር ነጥብ ተጋርቶ መውጣቱ ለዛሬው ጨዋታ መነቃቃትን ይፈጥርላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል። ከመመራት ተነስቶ ግብ ማስቆጠር የሚችሉ ተጫዋቾች የያዘው ቡድኑ እስከመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በወኔ መጫወታቸው በቀጣዮች ጨዋታዎች ከወራጅ ቀጠናው ሊያወጣቸው ይችላል ተብሎ ይታሰባል። በተከላካይ መስመር በሊጉ ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾች የያዘው ቡድኑ ወደ ድል ለመመለስ የፊት መስመሩን አጠናክሮ መግባት ግድ ይለዋል።

ቡድኖቹ በሊጉ አንደኛው ዙር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኝተው ያለ ግብ ተለያይተዋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዋሳ ከተማ

አርባ ነጥቦችን ሰብስበው ከሸገር ከተማ ጋር በግብ ክፍያ ተበልጠው አስራ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ፈረሰኞቹ ዳግም ወደ ድል ለመመለስ ሀዋሳ ከተማን ይገጥማሉ።

ባለፊት ስድስት ጨዋታዎች ሁለት አሸንፈው ሁለት ተሸንፈው ሁለቱን አቻ የወጡት ፈረሰኞቹ አዳማ ከተማን ካሸነፉ በኋላ ለሦስት ተከታታይ ሳምንታት ድል ማድረግ ተስኗቸው ከሰነበቱ በኋላ መቐለ 70 እንደርታን አሸንፈው ደግሞ ወደ ድል በተመለሱ ማግስት ሰላሳ ሁለተኛ ሳምንት ላይ ከወላይታ ድቻ ጋር ግብ ሳያስቆጥሩ ወጥተዋል። ከሊጉ መሪ እና ከጦና ንቦች  ጋር ነጥብ ተጋርቶ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሽንፈት አስተናግዶ አንድ ጨዋታ በማሸነፍ ማግኘት ካለበት አስራ ሁለት ነጥብ አምስት ብቻ ቢያሳካም በአራት ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ብቻ መሸነፉ ቡድኑ መጠነኛ መነቃቃት ላይ እንዳለ አመላካች ነው። ቡድኑን ለማጠናከር አዳዲስ ተጫዋቾቹን ወደ ስብስቡ ማቀላቀሉ የሚታወስ ሲሆን የወረቀት ጉዳዮችን ጨርሰው ለዛሬው ጨዋታ የሚሰለፉ ከሆነ ፈራሚዎቹ ቡድኑን ያግዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ፉክክሩ ይበልጥ እየጠነከረ በመጣው በሊጉ የዛሬውን ጨዋታ አሸንፈው ደረጃቸውን የማያሻሽሉ ከሆነ ቀጣይ ጨዋታዎች ከባድ እየሆኑ ስለሚሄዱ አሸንፈው ደረጃቸውን ማሸሻል እና ዳግም ወደ ድል መመለስ ይኖርባቸዋል።

አርባ አምስት ነጥቦችን በመሰበሰብ አምስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሐይቆቹ ካሸነፉ ረጅም ሳምንታት ስለተቆጠሩ ወደ ማሸነፍ ስነልቦና ለመመለስ ፈረሰኞቹ ጋር ይፋለማሉ።

በዋንጫ ፉክክር ላይ በንቃት ሲሳተፉ የነበሩት ሐይቆቹ ሳይጠበቁ ከፉክክሩ መውጣታቸው ቡድኑ የጎደለ ነገር እንዳለባቸው ማሳያ ነው። ለተከታታይ ዘጠኝ ሳምንት በአንድም ጨዋታ ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ያልቻለው ቡድኑ ምንም እንኳን ተከታታይ ሽንፈት ባያስተናግድም በአንዱ አቻ ሲወጣ በአንዱ እየተሸነፈ ወጥ የሆነ አቋሚ ላይ አይገኝም። ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ከ4ለ2 ሽንፈት በኋላ በጠባብ ግብ ልዩነት ሲሸነፍ የከረመው ቡድኑ ብዙ ግቦችን ካላስተናገዱ ቡድኖች ተርታ ይመደባል። ካለው ነጥብ መቀራረብ አንፃር አሁንም የዋንጫ ፉክክር ላይ መግባት የሚችል ዕድል ያለው ቡድኑ ዛሬ በማሸነፍ ወደ ድል የሚመለስ ከሆነ ከመሪዎቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ስለሚችል በማሸነፍ ስነልቦና ወደ ሜዳ ይገባል ተብሎ ይታመናል።

ቡድኖቹ በሊጉ 30 ጊዜ ተገናኝተው ፈረሰኞቹ 13 ሲያሸንፉ ሐይቆቹ 7 ጊዜ ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በቀሪዎቹ 10 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በግንኙነታቸው አጠቃላይ 65 ግቦች ሲቆጠሩ ፈረሰኞቹ 41 ሐይቆቹ ደግሞ 24 ግብ አስቆጥረዋል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ቅጣት እና ጉዳት ባይኖርም በቅርቡ ክለቡን የተቀላቀሉ የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች በዛሬው የመሳተፋቸው ነገር አጠራጣሪ ነው።

ኢትዮጵያ ቡና ከ ፋሲል ከነማ

አርባ ሦስት ነጥቦችን ሰብስበው ዘጠነኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ቡናማዎቹ ከመሪዎች ተርታ ለመሰለፍ አራተኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ዐፄዎቹ ጋር ይገናኛሉ።

25ኛው ሳምንት ላይ ድል ካደረጉ በኋላ ባለፉት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት ተስተካካዩን የደርቢን ጨዋታ ብቻ ነው። በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች አራቱን አቻ ወጥቶ በሁለቱ ሽንፈት ያስተናገደው ቡድኑ ሳይጠበቅ ወራጅ ቀጠና ላይ በሚገኙት በወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርስቲ እና በምድረ ገነት ሽረ ተሽንፏል። ዋንጫ ፉክክር ላይ ከሚገኘው መቻል ጋር አቻ መለያየቱ ቡድኑ ለመሪዎቹ እጅ የማይሰጥ መሆኑ ማረጋገጭ ቢሆንም ግብ አስቆጥሮ ነጥብ አስጠብቆ መውጣት አለመቻሉ መከላከሉ ላይ ያለውን ድክመት ያሳያል። ዛሬ የሚያደርጉትን ጨዋታ የሚያሸንፉ ከሆነ ነጥባቸውን ወደ 46 ከፍ በማድረግ ደረጃቸውን አሻሽለው ወደ ዋንጫ ፉክክር የሚገቡ ቢሆንም  ተጋጣሚያቸው ከእነሱ በሦስት ነጥብ ርቆ ከፍ ብሎ መቀመጡን ተከትሎ በጨዋታው ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በአርባ ስድስት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት ዐፄዎቹ ከመሪዎቹ ጋር ይበልጥ ለመጠጋት ቡናማዎቹን ይገጥማሉ።

27ኛው ሳምንት ላይ ወላይታ ድቻን ካሸነፈ በኋላ እስከ 31ኛው ሳምንት ድረስ ድል ማድረግ ያልቻለው ቡድኑ ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት አዳማ ከተማን ማሸነፉን ተከትሎ ለዛሬው ጨዋታ እንዲነሳሳ ያደርገዋል። ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ ተሸንፎ በአንዱ አቻ ወጥቶ አንድ ብቻ ያሸነፈው ፋሲል ሽንፈት ሲያስተናግድ ከአንድ በላይ ግቦችን ማስተናገዱ እና በሁለት ሁለት ግብ ልዩነት መሸነፉ ተከላከላይ መስመሩ የሳሳ ስለሆነ አስተካክሎ መቅረብ ይኖርበታል። በመጨረሻ ጨዋታም ቢሆን ሦስት ግቦችን ያስቆጠረው የአጥቂ መስመሩ በነበረው ጥንካሬ ማስቀጠል እንዳለበት ይታመናል። ከተከታታይ ሽንፈት በኋላ በሰፊ ግብ ልዩነት ማሸነፉ ከፍ ባለ ተነሳሽነት ለዛሬው ጨዋታ በመቅረብ ከመሪዎቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ይረዳቸዋል።

በሊግ ደረጃ 18 ጊዜ ተገናኝተው 6 ጊዜ ቡናማዎቹ ማሸነፍ ሲችሉ ዐፄዎቹም እንዲሁ 6 አሸንፈው ቀረዎቹን 6 ጨዋታዎች አቻ ሲለያዩ 35 ግቦች በግንኙነታቸው ወቅት መረብ ላይ ሲያርፉ ቡናማዎቹ 18 ግብ በማስቆጠር በላይነት የወሰዱ ሲሆን 17 ግቦችን ደግሞ ፋሲሎች አስቆጥረዋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከ ድሬዳዋ ከተማ

አርባ አምስት ነጥብ ሰብስቦ በግብ ክፍያ ተበልጦ ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀመጡት ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ወራጅ ላይ ከሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ጋር ይፋለማል።

በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች ሁለቱን አሸንፎ ሦስት ተሸንፎ ባንዱ አቻ የወጣው ቡድን 27ኛው ሳምንት ላይ አዳማ ከተማን ካሸነፈ በኋላ ለተከታታይ ሳምንት ሽንፈት ካስተናገደ በኋላ ፋሲል ከነማን በማሸነፍ ወደ ድል መመለስ የቻለ ቢሆንም ባሳለፍነው ጨዋታ ሳምንት ከወልዋሎ ጋር ሽንፈት አስተናግዶ ከደረጃ ዝቅ ብሏል። አሁንም ወደ ዋንጫ ፉክክር የመግባት ሰፊ እድል ያለው ቡድኑ ብዙ ግቦች የማያስተናግድ አንፃራዊ ብዙ ግብ ማስቆጠር የሚችል ቡድን መሆኑ እንደ ጠንካራ ጎን ይነሳል። ዛሬ ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኘውን ቡድን ከመግጠሙ አኳያ በመጨረሻ ሳምንት ከገጠመው ሽንፈት አገግሞ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይረዳዋል ተብሎ ቢታሰብም ተጋጣሚው ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትንቅንቅ ቀላል ጨዋታ አይሆንላቸውም።

ሠላሳ አራት ነጥብ ብቻ በመሰብሰብ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ውስጥ የተቀመጡት ብርቱካናማዎቹ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ይገናኛሉ።

በመጨረሻዎቹ ስድስት ጨዋታዎች በአንድም ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለው ቡድኑ በተለየም አሰልጣኛቸውን በቅጣት ካጡ በኋላ ለከፍተኛ ውጤት ቀውስ ተዳርገዋል። አራት ጨዋታዎችን ተሸንፈው በሁለት ጨዋታ ብቻ አቻ የወጡት ብርቱካናማዎቹ በቀላሉ ግብ ከሚቆጠርባቸው ቡድኖች ተርታ የሚመደብ ሲሆን በሲዳማ ቡና ፣ በነጌሌ አርሲ እና በባህር ዳር ከተማ ከሁለት በላይ ግቦች ተቆጥሮባቸው ለሽንፈት ተዳርገዋል። ለዚህም ቡድኑ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በመከላከሉ ላይ ያለቸውን ከፍተት በመቅረፍ ማጥቃት ላይም ጠንከር ብለው መግባት ይኖርባቸዋል። ከጨዋታ ጨዋታ ወደ ታች እየወረደ ያለው ቡድኑ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት ተጋጣሚው በጥሩ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቢሆንም የዛሬውን ጨዋታ ግዴታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።

16 ጊዜ በሊጉ የተገናኙት ቡድኖቹ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 6 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ 5 ያሸነፈ ሲሆን 5 ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል። 29 ግቦች ሲቆጠሩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 17 ግቦችን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 12 ግቦችን ተጋጣሚው መረብ ላይ አሳርፏል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ በቅጣትም ሆነ በጉዳት የሚያጣው ተጫዋች የሉም። ድሬዳዋ ከተማ አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለን ከስድስት ጨዋታዎች ቅጣት በኋላ ዛሬ ሲያገኝ በተጫዋቾች በኩል ግን አህመድ ረሺድን በቅጣት አቡበከር ሻሚልን ደግሞ በጉዳት ምክንያት ከዛሬው ሰብስብ ውጪ አድርጓል።