በ33ኛው ሳምንት መክፈቻ በነበረው ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ከ ወላይታ ዲቻ እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያደረጉት ጨዋታ ያለግብ ዜሮ ለ ዜሮ በሆነ ውጤት ተጠናቋል::

ኢትዮጵያ መድን ከ ወላይታ ዲቻ
በኢትዮጵያ መድን እና ወላይታ ድቻ መካከል የተደረገው የመጀመሪያው አጋማሽ ፍልሚያ በሁለቱም ወገኖች በኩል ጥንቃቄ የሰፈነበትና የተቀዛቀዘ ነበር። መድኖች ከተከላካይ መስመር በመነሳት ሜዳውን ሰንጥቀው በሚገቡ ቀጥተኛ ኳሶች የባላጋራቸውን ክልል ለመስበር ሲጥሩ በአንጻሩ ወላይታ ድቻዎች ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ረዣጅም ኳሶች ግብ ፍለጋ ተንቀሳቅሰዋል። ሆኖም ግን የሁለቱም ቡድኖች ስልት በሜዳው የመጨረሻው ሲሶ ላይ ፍሬያማ መሆን ባለመቻሉ የጠራ የግብ ሙከራ ሳይታይበት አጋማሹ በባዶ ለባዶ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽም ልክ እንደ መጀመሪያው ሁሉ በሁለቱም ወገኖች በኩል የተቀዛቀዘ እና የማጥቃት ተነሳሽነት የጎደለው ነበር ጨዋታውም በርካታ ስህተቶችና መቆራረጦች በዝተውበት ቀጥሏል። ሆኖም የመደበኛው ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃዎች ላይ ጨዋታውን ለማጠናቀቅ የዕለቱ ዳኛ ፊሽካቸው በሚጠበቅበት ሰዐት የወላይታ ድቻው ቅዱስ ቂርቆስ እጅግ አስከፊ ለሆነ ጉዳት ተዳርጓል። ይህንኑ ተከትሎ ተጫዋቹ አስቸኳይ የህክምና ዕርዳታ ለማግኘት ወዲያውኑ ወደ ህክምና ተቋም እንዲያመራ ተደርጓል። ጨዋታውም ያለግብ ዜሮ ለዜሮ በሆነ የአቻ ውጤት ተጠናቋል።
ሀዲያ ሆሳዕና ከ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
በሀዲያ ሆሳና እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መካከል የተደረገው የመጀመሪያው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ጥንቃቄን መርጠው የራሳቸውን የግብ ክልል በማጠናከር የተጫወቱበት ነበር። የንግድ ባንክ ስብስብ በመስመር አጥቂዎቻቸው አማካኝነት የባላጋራቸውን የተከላካይ ክፍል ለመስበር ሲጥሩ በአንጻሩ ሆሳናዎች ከጀርባ በሚነሱ ተሻጋሪ ኳሶች ግብ ለመፈለግ ተንቀሳቅሰዋል። በአጋማሹ 26ኛ ደቂቃ ላይ ዘላለም አበበ መሬት ለመሬት አክርሮ በመምታት ለግብ የቀረበ አስቆጪ ሙከራ ቢያደርግም በግብ ጠባቂው ብቃት ሊከሽፍ ችሏል። ከዚያ ውጭ በሁለቱም ወገን የጠራ ዕድል ሳይፈጠር አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲቀጥል በአንፃራዊነት ራሳቸውን አሻሽለው ወደ ሜዳ የተመለሱት ሀድያ ሆሳናዎች በማጥቃቱ ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ በንግድ ባንክ የግብ ክልል ላይ ተከታታይ ጫናዎችን መፍጠር ችለዋል። በተለይም በ77ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ ብሩክ በየነ በግንባሩ ገጭቶ ግሩም ሙከራ ቢያደርግም በባንክ ግብ ጠባቂና በግቡ አግዳሚ ትብብር ሊመለስበት ችሏል።

ከአንድ ደቂቃ በኋላም 78ኛው ደቂቃ ላይ ሆሳናዎች ወደ ሳጥን ይዘውት የገቡትን አደገኛ ኳስ የባንኩ ግብ ጠባቂ ሲመልሰው የተመለሰውን ኳስም ተከላካዮቹ ተረባርበው በማውጣት ከግብነት አድነዋታል። ከእነዚህ አስቆጪ ሙከራዎች ውጭ ጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል ግብ ሳይቆጠርበት በመጀመሪያው አጋማሽ በነበረው ዜሮ ለ ዜሮ ውጤት ፍጻሜውን አግኝቷል።

