ሪፖርት | የጣና ሞገዶች እና ጦሩ ነጥብ ተጋርተዋል

ሪፖርት | የጣና ሞገዶች እና ጦሩ ነጥብ ተጋርተዋል

መቻል ከባህር ዳር ከተማ ጋር 1ለ1 በመለያየት ከሊጉ መሪ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ የሚችልበትን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

በአዳማ የተደረገው የጨዋታ ሳምንቱ ቀዳሚው መርሐግብር ባህር ዳር ከተማን ከመቻል ያገናኘ ሲሆኑ ጦሩ ጨዋታውን በመቆጣጠር ጅማሮውን ለማድረግ ሲጥር የጣና ሞገዶች በፈጣን ሽግግር መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። 4ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገብረሚካኤል በተከላካዮች መካከል ያሻገረለትን ኳስ አንተነህ ተፈራ በጥሩ ቅልጥፍና በመውጣት በግሩም አጨራረስ መረብ ላይ አሳርፎ ቀዳሚ አድርጓቸው በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት እራሱ ድጋሚ ኳስ አግኝቶ ከግብ ጠባቂው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀም የቀረው ተጨማሪ ግብ ለማግኘት የተቃረቡበት አስቆጪው አጋጣሚ ይታወሳል።

የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የነበራቸው መቻሎች በተደጋጋሚ የጣና ሞገዶችን ግብ ጠባቂ ሲፈትኑ እያስተዋልን ጨዋታው ቀጥሎ የአጋማሹ መገባደጃ ላይ በረከት ደስታ ከግብ ጠባቂው ፊት ለፊት ተገናኝቶ ፔፔ ሰይዶ በጥሩ ቅልጥፍና የያዘበት ወርቃማው አጋጣሚ አቻ ሆነው ወደ መልበሻ ክፍል እንዲገቡ ሊያደርጋቸው የቀረበ ቢሆንም አጋማሹ በጣና ሞገዶች 1ለ0 መሪነት ተገባዶ ለእረፍት አምርተዋል።

ጨዋታው ከእረፍት ሲመለስ መቻሎች ጠንከር ብለው ሲመለሱ የጣና ሞገዶች ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት ወደኋላ አፈግፍገው በመጫወት ተመልሰዋል። ሁለተኛው የጨዋታ ክፍለጊዜ  እንደተጀመረ የጦሩ አብዱልከሪም ወርቁ በመስመር በኩል ኳስ ይዞ ገብቶ ያደረገው አደገኛው ሙከራ አቻ ሊያደርጋቸው የቀረበ ሲሆን ዘለግ ላለ ደቂቃ ሙሉ የጨዋታ በላይነት ወስደው የአቻነት ግብ ፍለጋ አጠናክረው መቀጠል የቻሉ ቢሆንም ጠንካራ ሙከራ ሳያደርጉ ቆይተው 83ኛው ደቂቃ ላይ ቸርነት ጉግሳ በግራ መስመር በኩል ኳስ ይዞ ሳጥን ውስጥ በሚገባበት ቅፅበት የጣና ሞገዶቹ ተከላካዮች በሰሩት ጥፋት ፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው ፈቱዲን ጀማል አስቆጥሮ አቻ አድርጓቸዋል።

ግቡ እንደተቆጠረ አማኑኤል ገብረሚካኤል ከእለቱ ዋና ዳኛ ጋር በነበረው ምልልስ በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ወጥቶባቸው ቀሪውን ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋች ለመጫዎት የተገደዱት የጣና ሞገዶች በሙሉ ኃይላቸው ወደ መከላከሉ ገብተው ተጨማሪ ግብ ሳያስተናግዱ ጨዋታው 1ለ1 ነጥብ በማጋራት ተቋጭቷል።