ሩዋንዳ እያስተናገደች በሚገኘው የ2016ቱ የአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተሳትፎ በምድቡ በአንድ ነጥብ የምድቡን የመጨረሻ ደረጃ ይዞ መሰናበቱ ይታወሳል፡፡
ብሄራዊ ቡድኑ አዲስ አበባ ከገባ በኀላ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ እና የቡድን መሪው አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ በቻን ቆይታቸው ዙርያ ዛሬ በ11፡00 በኢንተር ኮንትኔንታል አዲስ ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡
አሰልጣኝ ዩሀንስ ሳህሌ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ከተናገሩት አንኳር አንኳሩን መርጠን እንዲህ አቅርበናል፡፡
ስለ ዝግጅታቸው
” በቂ ባይሆንም ዝግጅት አድርገናል፡፡ እኛ ያደረግነው ዝግጅት በቂ እንዳልሆነ ያወቅነው በውድድሩ ላይ ተካፋይ ሆነን የሌሎች ሀገራትን አቋም ካየን በኃላ ነው፡፡ ከዚህም በፊት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ስለ ዝግጅት ማነስ ጉዳይ ተናግሬ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን እንደ ምክንያት ማቅረብ አልፈልግም፡፡ ከዚህ የተሻለ ወይም ረዘም ያለ ዝግጅት ብናደርግ ኖሮ የተሻለ እንጠቀም ነበር፡፡ ”
በውድድሩ ላይ ስለነበረው የጎል ማሰቆጠር ችግር
” ጎል የማግባት ችግር የሀገሪቱ ችግር ነው፡፡ ያሉን አጥቂዎች የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ እኛም ጎል የማግባቱን ችግር ሙሉ ለሙሉ በአጥቂዎቻችን ላይ አልጣልንም፡፡ ከአጥቂ ጀርባ የሚሰለፉትን ተጨዋቾች በተለይ የመሀል መስመር ተጨዋቾቻችን ከመሀል እየተነሱ ጎሎችን እንዲያስቆጥሩ አድርገናል፡፡ ለዛም ነው በመጨረሻው ጨዋታ ላይ የቀኝ መስመር ተከላካያችን ስዩም ጎሉን ያስቆጠረው፡፡ ሌላው ጎል ማስቆጠር የተቸገረንበት ምክንያት የተጋጣሚያችን የተከላካይ ክፍል ጠንካራ መሆን እንደ ዋንኛ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ”
የአሰልጣኝ መንበሩን ስለመልቀቅ
“ከዚህ በፊት ከነበረው የተሻለ ውጤት አምጥቻለው፡፡ የተሻለ ውጤት እስካመጣሁ ድረስ ከሃላፊነት አለቅም፡፡ ከዚህም በፊት የምለቀው ካለፈው የተሻለ ነገር ካላመጣው እንደሆነ ተናግሬያለሁ፡፡ ፌደሬሽኑ ያስቀመጠልኝ ግብ ለቻን ቡድኑን እንዳሳልፍ ነበር፡፡ እኔም ፌደሬሽኑ ያለኝን አድርጌያለው፡፡ ነገር ግን ቻን ላይ ባስመዘገብነው ውጤት አልረካውም፡፡ ከዚህ የተሻለ ነገር ብናመጣ ከዚህ የበለጠ እደሰት ነበር፡፡ በውድድሩ ያሉኝን ተጨዋቾች ለማሳየት ጥሬያለው ደግሞም ተጠቅሜበታለው፡፡ ”
ስለ ውጤቱ
“በውጤቱ አላዘንኩም፡፡ ነገር ግን አልረካሁም፡፡ ምክንያቱም ካገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር እኔ ከመጣው በኃላም ከኔ በፊትም ያለውን ነገር ሁላችንም እናቃለን፡፡ በዋነኝነት ባደረግናቸው ሶስቱም ጨዋታዎች ላይ ያሳየነው የመሻሻል ነገር አስደስቶኛል፡፡ በመጀመሪያው ጨዋታ ላይ ካደረግነው በተሻለ በሁለተኛው ጨዋታ ተንቀሳቅሰናል ከዛም በሶስተኛው ጨዋታ ከበፊቱ የተሻለ ተንቀሳቅሰናል፡፡ ይህን አይነት የመሻሻል ነገር በማሳየታችን ተደስቻለው፡፡
” እርግጥ ነው ተጋጣሚዮቻችን በልጠውናል፡፡ ነገር ግን ከኛ በተሻለ በእግር ኳሱ ላይ የሚሰሩት ቡድኖችን ነው የገጠምነው፡፡ ከነዚህ ቡድኖች ጋር ተጫውተን እንደዚህ አይነት ውጤት በማስመዝገባቸው ልናበረታታቸው ይገባል፡፡ ”
ቡድኑን ከያዙት በኃላ ያሳየው እንደ ጥሩ ሊጠቀስ የሚገባ ጉዳይ
” እንደ ጠንካራ ጎን የማየው የተጨዋቾቹን የዲሲፕሊን ጉዳይ ነው፡፡ እኔ ቡድኑን ከያዝኩት በኃላ እስካሁን ድረስ አንድ ቀይ ካርድ ብቻ ነው ያየነው፡፡ ወጣት ተጨዋቾችን ይዘን በ21 ጨዋታ አንድ ቀይ ካርድ ብቻ ማስመዝገብ እራሱ እንደ ጥሩ ጎን ሊጠቀስ የሚገባው ነገር ነው፡፡
“ከሁሉም በላይ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ብዙ ጨዋታዎችንን እያደረጉ ተጨዋቾቹ የመፍረክረክ ነገር አለማሳየታቸው እራሱ ተጨዋቾቹን ሊያስመሰግን የሚገባ ነገር ነው፡፡ “