“ፌዴሬሽኑ እየበጠበጠን ነው” ኢ/ር እታገኝ ዜና – የደቡብ ፖሊስ ህ/ግንኙነት ኃላፊ

ፌዴሬሽኑ በ2011 የውድድር ዘመን ከፕሪምየር ሊጉ የወረዱት መከላከያ፣ ደቡብ ፖሊስ እና ደደቢት ፌዴሬሽኑ በነሀሴ ወር ይፋ ባደረገው የፎርማት ለውጥ ምክንያት በሊጉ እንደሚቆዩ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም ለውጥ ተደርጎ ሊጉ በ16 ክለቦች እንዲቀጥል መወሰኑ አግባብ አይደለም ሲል ደቡብ ፖሊስ ቅሬታውን አቅርቧል፡፡

የክለቡ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኢንስፔክተር እታገኝ ዜና ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ለፕሪምየር ሊጉ ዝግጅት በማድረግ ላይ እያሉ የውሳኔ ለውጥ መደረጉ እንዳሳዘናቸው ተናግረዋል። “ፌዴሬሽኑ እየበጠበጠን ነው ፤ በ2012 በፕሪምየር ሊጉ ተሳታፊ ስለሆናችሁ ዝግጅት አድርጉ ተብለን በደብዳቤ ተፅፎልን፤ እኛም ያን ተከትለን ለፕሪምየር ሊግ እንዘጋጅ በሚል ነው ተጫዋቾችንም ሆነ አሰልጣኝ ያስፈረምነው። ለፕሪምየር ሊግ ነው ብለን ነው በጀትም የመደብነው። ለምሳሌ ዛሬ ልምምድ ላይ የመጡ ተጫዋቾች ይህን ውሳኔ ሰምተው ሳይሰሩ ቀርተዋል። በአጠቃላይ ፌዴሬሽኑ እኛ ላይ ችግር እየፈጠረ ነው። ፌዴሬሽኑ እየተከለ ያለው የሀሳብ መለዋወጥ በእጅጉ አሳዝኖናል።” ብለዋል።

ደቡብ ፖሊስ በጉዳዩ ዙርያ ለፌዴሬሽኑ ደብዳቤ እንደሚያስገባ ኢንስፔክተር እታገኝ ጨምረው ገልፀዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ