“ለፕሪምየር ሊጉ ነው እየተዘጋጀን ያለነው” ኮሎኔል ደረጀ መንግስቱ – የመከላከያ ክለብ ፕሬዝዳንት

ከ2011 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የወረደው መከላከያ በፎርማት ለውጡ ውሳኔ መሠረት ዘንድሮ በሊግ ተሳታፊነቱ እንደሚቀጥል ተገልፆ የነበረ ቢሆንም ፌዴሬሽኑ የውሳኔ ለውጥ አድርጎ 16 ክለቦች እንደሚካሄድ በማስታወቁ አሁን ባለው ሁኔታ በከፍተኛ ሊግ የሚወዳደር ይሆናል። ይህን ተከትሎም መከላከያ ይፋዊ የውሳኔ ለውጥ ከመጣ የራሱን እርምጃ እንደሚወስድ ተገልጿል።

መከላከያ በ2011 የውድድር ዘመን 14ኛ ደረጃን በመያዝ ከፕሪምየር ሊጉ ቢሰናበትም በወልዋሎ እና ሽረ ጨዋታ ቅሬታን በወቅቱ ለፌዴሬሽን ያስገባ ሲሆን ምላሽ ሳይሰጠው መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ፌዴሬሽኑ ለዘንድሮው የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ የውድድር ፎርማትን ማዘጋጀቱን በመግለፅ ለክለቡ በላከው ደብዳቤ በፕሪምየር ሊጉ እንደሚቀጥሉ እና ለዛም ዝግጅት እንዲያደርጉ መመሪያን በመስጠቱ ክለቡ ለሊጉ ዝግጅት ሲያደርግ እንደቆየ እና ተለዋጭ ሀሳቦች እየመጡ በመሆናቸው ክለቡ ወደ ወደራሱ እርምጃ ሊገባ እንደሚችል የክለቡ ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ደረጀ መንግስቱ ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግረዋል፡፡

ከወልዋሎ እና ሽረ ጨዋታ ጋር በተያያዘ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ እንዳላገኘ የገለፁት ፕሬዝዳንቱ መከላከያ ፌዴሬሽኑ በነሀሴ ወር መጀመርያ በሰጣቸው መመሪያ መሠረት ለፕሪምየር ሊግ ውድድር ሲዘጋጁ እንደቆየ ይናገራሉ። “በአዲሱ ፎርማት መሠረት በፕሪምየር ሊጉ ትሳተፋላችሁ ተብለን ነው እየተዘጋጀን የቆየነው። የተጫዋቾችንም ውል እያፀደቅን ያለነው በፕሪምየር ሊጉ መሠረት ነው። አሁንም ቢሆን እኛ በመረጃ ደረጃ ከሰማነው ውጪ ፌዴሬሽኑ ያለን አንድም ነገር የለም። እኛ እስካሁን የራሳችንን ሥራ ነው ስንሰራ የቆየነው። (በ24 ክለቦች መካአል እንዲካሄድ የተወሰነው ውሳኔ ስለመታጠፉ) የተወሰነው ውሳኔ ይሄ ነው በሚል የተገለፀልን ነገር የለም። ህጋዊ ሆኖ የመጣልን ውሳኔ ባይኖርም የሚለወጥ ነገር ከመጣ ግን የራሳችን ውሳኔ የምንወስን ይሆናል” ብለዋል።

ክለቡ ሊወስደው ስለሚችለው እርምጃ የተጠየቁት ፕሬዝዳንቱ ስለ እርምጃው ከመናገር የተቆጠቡ ሲሆን ይፋዊ ደብዳቤ ከፌዴሬሽኑ ሲደርሰው አቋማቸውን እንደሚያሳውቁ ገልፀውልናል።


© ሶከር ኢትዮጵያ