ወልቂጤ ከተማ ቶጓዊውን ግብ ጠባቂ ለማስፈረም ተስማማ

ከካሜሩናዊው ግብ ጠባቂ ቢሊንጌ ኢኖህ ጋር የተለያየው ወልቂጤ ከተማ ከሀዋሳው ሶሆሆ ሜንሳህ ጋር ከስምምነት ደርሷል።

ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ወልቂጤ በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው እየተመራ በሀዋሳ ግብርና ኮሌጅ ሜዳ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን እያከናወነ ይገኛል፡፡ ክለቡ ራሱን ለማጠናከር በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን እያስፈረመ ሲገኝ ባለፉት ሁለት ሣምንታት ደግሞ ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ሀገር ተጫዋቾች የሙከራ ጊዜን እየሰጠ ቆይቷል፡፡ በዚህም ባለፈው ዓመት የከፍተኛ ሊግ ውድድር ላይ ቋሚ ግብ ጠባቂው በመሆን ሲያገለግለው ከነበረው ካሜሮናዊው ቢሊንጌ ኢኒሆ ጋር ለመቀጠል ከስምምነት ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ፊቱን ወደ ሶሆሆ ሜንሳህ አዙሯል።

በአሻንቲ ጎልድ እና በሀገሩ ቶጎ ዲይቶ ለተባለ ክለብ የተጫወተው ይህ ግብ ጠባቂ በናይጄሪያው ኢኑጉ ሬንጀር ከቆየ በኋላ ወደ ጋቦኑ ሞናና ክለብ አምርቶ ነበር የሀገራችንን ሊግ የተቀላቀለው። ከወልቂጤ ከተማ ጋር ዛሬ ዝግጅት የጀመረው የ29 ዓመቱ ሜንሳህ ከሦስት ዓመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ከመጣ በኃላ በሀዋሳ ከተማ ቆይታን አድርጓል። ዘንድሮ ደግሞ በቅድመ ሁኔታዎች ከወልቂጤ ጋር መስማማት የሚችል ከሆነ ከአዲስ ፈራሚዎቹ ጆርጅ ደስታ እና ይድነቃቸው ኪዳኔ ጋር ለቋሚነት የሚፎካከር ይሆናል፡፡

በተያያዘ ዜናም ወልቂጤ ከተማ የቀድሞው የተከላካይ ስፍራ ተጫዋቹ ዐወል ከድርን የመለሰው ሲሆን ተጫዋቹ በቅርቡ ፊርማውን ያኖራል ተብሎም ይጠበቃል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ