የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የወዳጅነት ጨዋታ ሊያደርግ ነው

በአሰልጣኝ አብራሃም መብራቱ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በመጪው እሁድ በባህርዳር ዓለምአቀፍ ስታዲየም ከዩጋንዳ ጋር የወዳጅነት ጨዋታ ሊያደርግ ነው፡፡

በካሜሩን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የቻን ውድድር በመጪው ጥቅምት 8 ከሩዋንዳ ጋር ላለባቸው የመልስ ጨዋታ 24 ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅታቸውን በአዳማ የጀመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላት ለመልሱ ጨዋታ ወደ ሩዋንዳዋ ርዕሰ መዲና ኪጋሊ ከማምራታቸው በፊት በመጪው ሳምንት እሁድ በባህር ዳር ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በቀጠናው ጠንካራ ብሔራዊ ቡድንን መገንባት ከቻሉት “ክሬኖቹ” ጋር የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርጉ ይሆናል፡፡

ለቻን ለማለፍ ከመጨረሻው እና ፈታኙ ምዕራፍ ላይ የሚገኙት ዋሊያዎቹ በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ በትግራይ ዓለምአቀፍ ስታዲየም በሩዋንዳ 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት መረታታቸው ይታወሳል፡፡

ዩንዳዎች ለዚህ ጨዋታ ይረዳቸው ዘንድ በቅርቡ ሴባስትያን ዴሳብሬን በመተካት የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ተደርገው የተሾሙት ጆናታን ሚክንስትሪ ለ21 በውጪ ሀገራት ለሚጫወቱ ተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል፡፡ በዚህ የቡድን ስብስብ ውስጥ በቅርቡ ለጊኒው ኤሲ ሆሮያ ፊርማውን ያኖረው ሮበርት ኦዶንካራን ጨምሮ የቀድሞው ሌላኛው የፈረሰኞቹ የቀድሞ ጎል ዘብ ዴኒስ ኦንያንጎም ተካቷል፡፡

ከቀናት በፊት በይፋ የተሾሙት የሰሜን አይርላንዳዊዉ ጆናታን ከዚህ ቀደም በሴራሊዮን ፣ ሩዋንዳ ብሔራዊ ቡድን የሰሩ ሲሆን በ27 አመታቸው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድንን በአሰልጣኝነት ሲረከቡ የዓለማችን ወጣቱ የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ በመሆን ባለታሪክ መሆናቸው አይዘነጋም፡፡

የቡድኑ ተጫዋቾች ከጨዋታው ሁለት ቀን በፊት በአዲስ አበባ ተሰባስበው ወደ ባህርዳር የሚያቀኑ ይሆናል፡፡


© ሶከር ኢትዮጵያ