ኢትዮጵያ ቡና ተስፈኛውን ወጣት የግሉ ሊያደርግ ነው

የ2012 ቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በባቱ ከተማ እያደረገ የሚገኘው ኢትዮጵያ ቡና የወደፊት ተስፋኛ ተጫዋች መሆኑን እያሳየ የሚገኘውን ወጣት ለማስፈረም ተቃርቧል።

ከ2009 ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ ከ17 ዓመት በታች ቡድን መጫወት የጀመረው እና በዘንድሮ ዓመት ከ20 ዓመት በታች ቡድን አንድም በከፍተኛ ሊግ ከዋናውን ቡድን ጋር እየተመላለሰ በጥሩ ብቃት ሲያገለግል የቆየው ሬድዋን ናስር ለኢትዮጵያ ቡና ፊርማውን ለማኖር ተቃርቧል። ከኢትዮጵያ ቡና ጋር አብሮ ልምምድ እየሰራ የሚገኘው ሬድዋን በሜዳ ላይ በሚያደርገው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌን ማሳመን በመቻሉ በቅርቡ ድድርድሩ ተጠናቆ የሜዲካል ምርመራ በማድረግ በአረንጓዴ ቲሴራ የረዥም ዓመት ኮንትራት ይፈርማል ተብሎ ይጠበቃል።

የተከላካይ አማካዩ ሬድዋን ናስር ያለፉትን ሦስት ዓመት በእግርኳስ ህይወቱ ላይ ከፍተኛ እድገት በማሳየት የወደፊት ተስፈኛ ወጣት ተጫዋች መሆኑን ሲያሳይ በኢትዮጵያ ከ17 እና 20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ተደርጎለት የተጫወተ ሲሆን ዝውውሩ ከተጠናቀቀ ከታላቅ ወንድሙ አቡበከር ናስር ጋር በአንድ ቡድን አብሮ የመጫወት ዕድል የሚያገኝ ይሆናል። ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቡና መለያ እንደታዩት ወንድማማቾች ሚሊዮን በጋሻው እና አሸናፊ በጋሻው፣ አስራት ሸገሬ እና ሰብስቤ ሸገሬ፣ ስምዖን ዓባይ እና ዮርዳኖስ ዐባይ ሁሉ አቡበከር ናስር እና ሬድዋንም በኢትዮጵያ ቡና የተጫወቱ ወንድማማቾች ይሆናሉ።


© ሶከር ኢትዮጵያ